1 ሳሙኤል 15:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ሳኦል እኔን ትቶአል፤ ትእዛዜንም ስላልጠበቀ እርሱን በማንገሤ ተጸጸትሁ፤” ሳሙኤልም በዚህ ነገር ተቈጥቶ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ማለደ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ፤ እኔን ከመከተል ተመልሷልና፣ ትእዛዜንም አልፈጸመምና።” ሳሙኤልም እጅግ ተጨንቆ፣ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና፥ ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ።” ሳሙኤልም እጅግ ተቆጥቶ፥ ሌሊቱን ሁሉ ወደ ጌታ ጮኸ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ።” ሳሙኤልም አዘነ። ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቆጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኽ። |
በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር “እነርሱን በመፍጠሬ አዝኛለሁ፤ ስለዚህ እነዚህን የፈጠርኳቸውን ሰዎች፥ እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና ወፎችንም ጭምር ከምድር ላይ አጠፋለሁ” አለ።
የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ በሚዘጋጅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ መቅጣት ያለውን ውሳኔ ለውጦ ይቀሥፋቸው የነበረውን መልአክ “በቃህ! አቁም!” አለው፤ በዚህም ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ቆሞ ነበር።
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሁለት ጊዜ ተገልጦለት ባዕዳን አማልክትን እንዳያመልክ ያዘዘው ቢሆንም እንኳ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር አልታዘዘም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር እየራቀ ሄደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ተቈጣ፤
ሳኦል ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ ምክንያት ሞተ፤ እርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈጸመም፤ እንዲያውም የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን በመጠየቅ መመሪያ ለማግኘት ሞከረ እንጂ እግዚአብሔርን አልጠየቀም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አስተላለፈ።
ቀጥሎም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ መልአክ ልኮ ነበር፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ማጥፋት እንደ ጀመረ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያደረሰው ችግር አሳዝኖት መልአኩን “እስከ አሁን የደረሰባቸው ችግር ይበቃልና አቁም!” አለው። በዚያን ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።
ሙሴ ግን እግዚአብሔር አምላኩን በመማለድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በሥልጣንህና በታላቅ ኀይልህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን ሕዝብህን እስከዚህ የምትቈጣው ስለምነው?
እኔ ያዘዝኳቸውን ለመፈጸም እምቢ ይሉ እንደ ነበሩት እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኃጢአት ይሠራሉ፤ ባዕዳን አማልክትን ያመልካሉ፤ እስራኤልና ይሁዳ በአንድነት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋል።
አናዳምጥም ብትሉ ግን ስለ ትዕቢታችሁ ተደብቄ አለቅሳለሁ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምርኮኞች ሆነው በመወሰዳቸውም ምርር ብዬ አለቅሳለሁ፤ እንባዬም ባለማቋረጥ ይፈስሳል።
ነገር ግን እንደገና ሐሳባችሁን በመለወጥ ስሜን የሚያስነቅፍ ሥራ ሠራችሁ፤ ይኸውም ሁላችሁም እንደየፍላጎታቸው ነጻ የለቀቃችኋቸውን እንደገና ባሪያዎች አድርጋችሁ መግዛት ቀጠላችሁ።
“ነገር ግን ደግ ሰው መልካም ማድረጉን ትቶ ክፉ ሰዎች የሚያደርጉአቸውን ክፉና አጸያፊ ነገሮች ማድረግ ቢጀምር፥ በሕይወት መኖር የሚችል ይመስላችኋልን? አይደለም! እንዲያውም ያደረገው የደግነት ሥራ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ባለመታመኑና ኃጢአተኛም በመሆኑ ምክንያት ይሞታል።
እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ያደረጉትንና ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውን ተመለከተ፤ ስለዚህም ራርቶላቸው በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን ቅጣት አልፈጸመም።
እንዲህም ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን እንደምታደርግ ገና በአገሬ ሳለሁ ተናግሬ አልነበረምን? ከፊትህ ኰብልዬ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ያቀድኩትም በዚህ ምክንያት ነበር፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅር የተመላህ፥ ቊጣህን መልሰህ ምሕረት የምታደርግ አምላክ መሆንህን ዐውቅ ነበር።
እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁ በጎ አድርጉ፤ ክፉ ለሚያደርጉባችሁና ለሚያሳድዱአችሁ ጸልዩ” እላችኋለሁ።
“የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚለው እንዲህ ነው፦ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ ያላችሁን እምነት እንዴት ታጓድላላችሁ? ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራት ከእግዚአብሔር ርቃችኋል፤ በእርሱም ላይ ዐምፃችኋል፤
ሳሙኤልም ሲመልስለት እንዲህ አለው፤ “ይህ የሞኝነት አሠራር ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልፈጸምክም፤ ትእዛዙን ብትፈጽም ኖሮ አንተና ዘሮችህ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንድትነግሡ ዛሬ መንግሥትህን ባጸናልህ ነበር፤
ሄደህ በዐማሌቃውያን ላይ አደጋ በመጣል ያላቸውን ሁሉ ደምስስ፤ ከእነርሱ ምንም ነገር አታስቀር፤ ወንዶችን፥ ሴቶችን፥ ልጆችንና ሕፃናትን፥ ከብቶችን፥ በጎችን፥ ግመሎችንና አህዮችን ሁሉ ግደል።”
ከዚያን ሰዓት ጀምሮ ሳሙኤል በነበረበት ጊዜ ሁሉ ንጉሥ ሳኦልን በዐይኑ አላየውም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጽቶ ስለ ነበር፥ ለእርሱ በማዘን ያለቅስለት ነበር።
ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ የአጋግን ሕይወት አተረፉ፤ እንዲሁም ምርጥ ምርጥ የሆኑትን በጎችና የቀንድ ከብቶች፥ የሰቡ ሰንጋዎችንና ጠቦቶችን ከዚህም ጋር መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አላጠፉም፤ እነርሱም ያጠፉት የማይረባውንና የማይጠቅመውን ነገር ብቻ ነበር።
እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ከንጉሥነት ስለ ሻርኩት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ድረስ ነው? እኔ እርሱ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖር ዘንድ አልፈልገውም። ይልቅስ የወይራ ዘይት በቀንድ ሞልተህ በመያዝ በቤተልሔም ወደሚኖረው እሴይ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ዘንድ ሂድ፤ እኔ ከእርሱ ልጆች መካከል አንዱን ንጉሥ እንዲሆን መርጬአለሁ።”