Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት

1 ሳኦል ሲነግሥ ዕድሜው 30 ዓመት ነበር፤ በእስራኤልም ላይ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት

2 ከእስራኤል ሕዝብ መካከል የተውጣጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን መረጠ፤ ከእነርሱ መካከል ሁለቱን ሺህ በሚክማስና በቤትኤል በሚገኘው ኮረብታማ አገር ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ መደበ፤ አንዱን ሺህ ሰዎች ደግሞ ከልጁ ከዮናታን ጋር በማሰለፍ በብንያም ነገድ ግዛት ውስጥ ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ኮረብታማ አገር ላከ፤ ከዚህ የተረፉትን ሌሎች ሰዎች ግን ወደየቤታቸው አሰናበተ።

3 ዮናታን ጌባዕ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ጣለ፤ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ይህን ወሬ ሰሙ፤ ሳኦልም መልእክተኞችን ልኮ በሀገሩ ሁሉ እምቢልታ በማስነፋት ዕብራውያን ለጦርነት ጠራ።

4 ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ድል እንዳደረገ እስራኤላውያን ሰሙ፤ እስራኤላውያንም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ የተጠሉ መሆናቸውን ዐወቁ፤ ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ከሳኦል ጋር የሚሰለፉ መሆናቸውን ለመግለጥ በጌልገላ ተሰበሰቡ።

5 ፍልስጥኤማውያንም እስራኤላውያንን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ እነርሱም ከሠላሳ ሺህ የጦር ሠረገሎችና ከስድስት ሺህ ፈረሰኞች ጋር ብዛቱ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛ ሠራዊት ነበራቸው፤ ሄደውም በቤትአዌን በስተምሥራቅ ሚክማስ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መሸጉ።

6 እስራኤላውያን ሁኔታው አስጊ መሆኑን ባዩና ሠራዊቱም መዋከቡን በተመለከቱ ጊዜ በዋሻ፥ በሾኽ ቊጥቋጦ፥ በአለቶች መካከል በጒድጓዶችና በጒድባ ውስጥ ተሸሸጉ፤

7 ከዕብራውያን መካከል አንዳንዶቹ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ግዛቶች ሄዱ። ሳኦል ግን እስከዚህ ጊዜ ድረስ በጌልገላ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሠራዊት ከፍርሃት የተነሣ ይንቀጠቀጥ ነበር፤

8 እንዲሁ ያደርግ ዘንድ ሳሙኤል ባዘዘው መሠረት፤ ሳኦል እስከ ሰባት ቀን ድረስ የሳሙኤልን መምጣት ሲጠብቅ ቈየ፤ ይሁን እንጂ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሳሙኤል ወደ ጌልጌላ አልመጣም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ የሳኦል ሰዎች ሳኦልን በመክዳት ማፈግፈግ ጀመሩ፤

9 ስለዚህም ሳኦል ሕዝቡን “የሚቃጠለውንና ለደኅንነት የሚሆነውን የአንድነት መሥዋዕት አምጡልኝ” ብሎ በማዘዝ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።

10 ይህንንም መሥዋዕት የማቅረቡን ሥርዓት እንደ ፈጸመ ወዲያውኑ ሳሙኤል ደረሰ፤ ሳኦልም ወጥቶ አቀባበል አደረገለት፤

11 ሳሙኤል ግን “ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሕዝቡ ሊከዱኝ ተቃርበው ነበር፤ አንተም በቀጠርከኝ ሰዓት ሳትመጣ ቀረህ፤ ከዚህም በላይ ፍልስጥኤማውያን መጥተው በሚክማስ ተሰለፉ፤

12 ስለዚህም ‘ፍልስጥኤማውያን ገና በጌልገላ ሳለሁ አደጋ ሊጥሉብኝ ነው የእግዚአብሔርንም ርዳታ ገና አለመንኩም’ ብዬ አሰብኩ፤ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚገባኝም ተረዳሁ።”

13 ሳሙኤልም ሲመልስለት እንዲህ አለው፤ “ይህ የሞኝነት አሠራር ነው፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልፈጸምክም፤ ትእዛዙን ብትፈጽም ኖሮ አንተና ዘሮችህ በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም እንድትነግሡ ዛሬ መንግሥትህን ባጸናልህ ነበር፤

14 አሁን ግን መንግሥትህ ዘላቂ አይሆንም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ ስላልጠበቅህ እርሱን በሕዝቡ ላይ መሪ ይሆን ዘንድ ቀብቶታል።”

15 ሳሙኤልም ከጌልጌላ ተነሥቶ ሄደ፤ ሳኦልም ከወታደሮቹ ጋር ለመደባለቅ ሲሄድ የቀሩት ሰዎች ተከተሉት፤ ከጌልገላም ተነሥተው በብንያም ግዛት ወደምትገኘው ወደ ጊብዓ ሄዱ፤ ሳኦልም ሠራዊቱን በቈጠረ ጊዜ ብዛታቸው ስድስት መቶ ሆኖ ተገኘ፤

16 ሳኦል፥ ልጁ ዮናታንና ሠራዊታቸው በብንያም ግዛት ውስጥ ጌባዕ ተብላ በምትጠራው ስፍራ መሸጉ፤ የፍልስጥኤማውያን ወታደሮችም ምሽግ በሚክማስ ነበር፤

17 የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በሦስት ክፍል ተከፍለው ወረራ ለማድረግ ከምሽጋቸው ወጡ፤ አንዱ ቡድን በሹዓል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቅጣጫ አመራ፤

18 ሁለተኛው ቡድን ወደ ቤትሖሮን ሲሄድ፥ ሦስተኛው ቡድን ከጸቦዒም ሸለቆና ከምድረ በዳው ፊት ለፊት ወደሚገኘው ጠረፍ አለፈ።

19 ዕብራውያን ሰይፍና ጦር እንዳይሠሩ ፍልስጥኤማውያን ቊጥጥር ያደርጉባቸው ስለ ነበር በዚያን ዘመን በእስራኤል ብረት አቅልጠው የሚሠሩ ጠቢባን አልነበሩም፤

20 እንዲሁም እስራኤላውያን ማረሻቸውንና ዶማቸውን ለማሾል፥ መጥረቢያቸውንና ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን መውረድ ነበረባቸው፤

21 መጥረቢያ ለማሳልና የበሬ መንጃ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ አራት ግራም ያኽል የሚመዝን ጥሬ ብር ነበር፤ ማረሻና ዶማ ለማሾልም የሚከፈለው ዋጋ የዚሁ እጥፍ ነበር።

22 ከዚህም የተነሣ በጦርነቱ ቀን ከሳኦልና ከልጁ ከዮናታን በቀር በእስራኤላውያን ወታደሮች መካከል ሰይፍና ጦር የያዙ አልነበሩም።

23 ፍልስጥኤማውያን የሚክማስን መተላለፊያ የሚቈጣጠር አንድ ቡድን ላኩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos