ዮናስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየዮናስ ብስጭትና የእግዚአብሔር ምሕረት 1 ዮናስ በዚህ ነገር ስላልተደሰተ ተበሳጨ፤ 2 እንዲህም ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፦ “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ይህን እንደምታደርግ ገና በአገሬ ሳለሁ ተናግሬ አልነበረምን? ከፊትህ ኰብልዬ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ያቀድኩትም በዚህ ምክንያት ነበር፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽና ምሕረትህ የበዛ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅር የተመላህ፥ ቊጣህን መልሰህ ምሕረት የምታደርግ አምላክ መሆንህን ዐውቅ ነበር። 3 አሁንም ጌታ ሆይ! እባክህ ግደለኝ፤ ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል።” 4 እግዚአብሔርም “ይህን ያኽል ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው። 5 ዮናስም ከከተማይቱ ወጥቶ ከከተማይቱም በስተ ምሥራቅ በኩል ዳስ በመሥራት ከጥላው ሥር ተቀመጠ፤ በዚያም ሆኖ በነነዌ ላይ የሚደርሰውን ነገር ይጠባበቅ ነበር። 6 ጥላ በማግኘት ከፀሐይ ግለት እንዲድን እግዚአብሔር አምላክ አንድ የቅል ተክል አብቅሎ ቅጠሎችዋ ከዮናስ ራስ በላይ እንዲሆኑ አደረገ፤ ዮናስም ከቅሉ ሐረግ ጥላ በማግኘቱ እጅግ ተደሰተ። 7 ነገር ግን በማግስቱ ጠዋት እግዚአብሔር አንድ ትል አዘጋጀ፤ ትልዋም ቅሊቱን በላች፤ እርሷም ደረቀች። 8 ፀሐይ ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ ላከ፤ የፀሐዩም ሐሩር ራሱን ስላቃጠለው ዮናስ ተዝለፈለፈ፤ ሞትንም በመመኘት “ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል” አለ። 9 እግዚአብሔርም “ስለዚህች ቅል ልትበሳጭ ይገባሃልን?” አለው። ዮናስም “በእርግጥ መበሳጨት ይገባኛል፤ እንዲያውም በንዴት እስከምሞት ድረስ መበሳጨት አለብኝ!” አለ። 10 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፦ “አንተ በአንድ ቀን በቅላ፥ በአንድ ቀን ለደረቀች፥ እንዲያውም ላልደከምክባትና ላላሳደግሃት ተክል ይህን ያኽል አዝነሃል! 11 ነነዌ ክፉና ደጉን የማይለዩ ከአንድ መቶ ኻያ ሺህ ሕዝብ በላይ የሚኖሩባት ከተማ ነች፤ ብዙ እንስሶችም አሉባት፤ ታዲያ እኔ ለዚህች ታላቂቱ ከተማ አልራራምን?” |