መዝሙር 110 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር የመረጠው ንጉሥ 1 እግዚአብሔር ለጌታዬ (ለመሲሑ) “ጠላቶችህን በእግርህ ማረፊያ ሥር እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው። 2 እግዚአብሔር ኀያል ገዢነትህን ከጽዮን አንሥቶ ያሰፋዋል፤ እንዲህም ይልሃል፦ “በጠላቶችህ ላይ ንገሥ።” 3 መግዛት በምትጀምርበት ቀን ሕዝብህ ይገዙልሃል፤ የተቀደሰውን መጐናጸፊያ ደርበህ ከአጥቢያ ኮከብ በፊት እንደ ጠል ወለድኩህ። 4 እግዚአብሔር “በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘለዓለም ካህን ትሆናለህ” ብሎ ማለ፤ መሐላውም የማይሻር ነው። 5 እግዚአብሔር በቀኝህ ነው፤ በሚቈጣበት ጊዜ ነገሥታትን ድል ነሥቶ ይሰባብራቸዋል። 6 በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ የጦር ሜዳዎችንም ሬሳ በሬሳ ያደርጋል፤ በምድር ላይ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ይደመስሳል። 7 ንጉሡ ከመንገድ ዳር ካለው ምንጭ ከጠጣ በኋላ፥ ኀይሉን በማደስ በድል አድራጊነት ጸንቶ ይቆማል። |