Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከተልባ ቃጫ የተሠራ መታጠቂያ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ከበፍታ የተሠራ መታጠቂያ ገዝተህ ታጠቀው፤ ውሃ ግን አታስነካው።”

2 ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት መታጠቂያውን ገዝቼ ታጠቅሁት፤

3 እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦

4 “ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ሂድና መታጠቂያውን በአለት ንቃቃት ውስጥ ደብቀው።”

5 ስለዚህ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ሄጄ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መታጠቂያውን ደበቅሁት።

6 ከብዙ ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር፥ “ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ተመልሰህ ሂድና መታጠቂያውን ውሰድ” አለኝ።

7 እኔም ሄጄ መታጠቂያውን የደበቅሁበትን ስፍራ አገኘሁ፤ መታጠቂያውንም ባየሁት ጊዜ ተበላሽቶና ከጥቅም ውጪ ሆኖ አገኘሁት።

8 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

9 “የይሁዳን ኲራትና የኢየሩሳሌምን ታላቅ ትዕቢት የማስወግደው በዚህ ዐይነት ነው፤

10 እነዚህ በክፋት የተሞሉ ሕዝብ ለእኔ መታዘዝን እምቢ ብለዋል፤ ከምንጊዜውም ይልቅ እልኸኞች ሆነዋል፤ ባዕዳን አማልክትን በማምለክ ያገለግላሉ፤ ከዚህም የተነሣ እነርሱ ዋጋቢስ ሆኖ እንደ ቀረው እንደዚያ መታጠቂያ ይሆናሉ።

11 መታጠቂያ በወገብ ዙሪያ ተጣብቆ እንደሚገኝ፥ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ከእኔ ጋር እንዲጣበቁ ዐቅጄ ነበር፤ ይህንንም ያደረግኹት ሕዝቤ እንዲሆኑና ለስሜ ምስጋናና ክብር እንዲያስገኙ ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙኝም።”


የወይን ጠጅ ማድጋ

12 እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! ‘እያንዳንዱ ማድጋ በወይን ጠጅ የተሞላ ይሆናል’ ብለህ ለእስራኤል ሕዝብ ንገር፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ ‘ማድጋ በወይን ጠጅ መሞላቱን የማናውቅ ይመስልሃልን?’ ይሉሃል።

13 ከዚህ በኋላ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ እስከሚሰክሩ ድረስ በወይን ጠጅ ልሞላቸው እንዳቀድኩ ንገራቸው፤ በዚያን ጊዜ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡ ነገሥታትን፥ ካህናትን፥ ነቢያትንና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችን ሁሉ በወይን ጠጅ አሰክራቸዋለሁ።

14 ያን ጊዜ አባቶችንና ልጆቻቸውን ሁሉንም እንደ ማድጋ እርስ በርሳቸው አጋጫቸዋለሁ፤ ምንም ዐይነት ሐዘኔታ፥ ርኅራኄ ወይም ምሕረት እነርሱን ከማጥፋት ሊያግደኝ አይችልም።”


ስደት እንደሚመጣ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

15 እግዚአብሔር ተናግሮአልና፤ ትዕቢታችሁን አስወግዳችሁ ስሙት፤ በጥንቃቄም አድምጡት።

16 ጨለማን አምጥቶ በተራራዎች ከመሰናከላችሁ በፊት ተስፋ ያደረጋችኹትን ብርሃን ወደ ድቅድቅ ጨለማና ወደ ጥልቅ ጭጋግ ከመለወጡ በፊት አምላካችሁን እግዚአብሔርን አክብሩ።

17 አናዳምጥም ብትሉ ግን ስለ ትዕቢታችሁ ተደብቄ አለቅሳለሁ፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምርኮኞች ሆነው በመወሰዳቸውም ምርር ብዬ አለቅሳለሁ፤ እንባዬም ባለማቋረጥ ይፈስሳል።

18 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የተከበረ ዘውዳቸው ከራሳቸው ስለ ወደቀ ንጉሡና ንግሥት እናቱ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ ንገራቸው።

19 በደቡብ ይሁዳ ያሉት ከተሞች በጠላት ስለ ተከበቡ ማንም ወደ እነርሱ ሊሄድ አይችልም፤ መላው የይሁዳ ሕዝብ ተማርከው ይወሰዳሉ።”

20 ኢየሩሳሌም ሆይ! ከሰሜን በኩል የጠላቶችሽን አመጣጥ ተመልከቺ፤ ስትንከባከቢያቸው የነበርሽና መመኪያዎችሽ የነበሩ ሕዝብ የት ደረሱ?

21 ወዳጆች ብለሽ ያቀረብሻቸው ወራሪዎችሽና ገዢዎችሽ ሲሆኑ ምን ትያለሽ? በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ሕመም አይሰማሽምን?

22 ይህ ሁሉ የደረሰብኝ ለምንድነው? “ልብሴስ ተቀዶ የተደፈርኩት ስለምንድነው?” ብለሽ ብትጠይቂ፤ ይህ ሁሉ የደረሰብሽ ኃጢአትሽ እጅግ የከፋ በመሆኑ ምክንያት እንደ ሆነ ዕወቂ።

23 ኢትዮጵያዊ መልኩን፥ ነብርም ዝንጒርጒርነቱን መለወጥ አይችልም፤ እንዲሁም እናንተ ክፉ ነገር ማድረግን ስለ ለመዳችሁ ደግ ሥራ መሥራት አይሆንላችሁም።

24 አሁን ግን እግዚአብሔር የበረሓ ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው ገለባ ይበታትናችኋል።

25 ዕድል ፈንታችሁም ይህ እንደሚሆን እግዚአብሔር ተናግሮአል። እርሱን ረስታችሁ በሐሰተኞች አማልክት ስለ ታመናችሁ በእናንተ ላይ ይህን ለማድረግ ወስኖአል።

26 እግዚአብሔር ራሱ ልብሳችሁን ገፎ ኀፍረተ ሥጋችሁ እንዲጋለጥ ያደርጋል።

27 እርሱ የሚጠላውን ነገር ስታደርጉ አይቶአችኋል፤ ከባልንጀራው ሚስት ጋር ለማመንዘር እንደሚጐመጅ ሰውና ባዝራ እንደሚፈልግ ሰንጋ ፈረስ፥ እናንተም የአሕዛብ አማልክትን ተከትላችሁ በየኰረብታው ራስና በየሜዳው ስትኳትኑ አይቶአችኋል። የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፥ ወዮላችሁ፥ ከቶ ንጹሕ መሆን የምትችሉት መቼ ይሆን?

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos