2 ሳሙኤል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት የሕዝብ ቈጠራ ማድረጉ ( 1ዜ.መ. 21፥1-27 ) 1 እግዚአብሔር እንደገና በእስራኤል ላይ ስለ ተቈጣ በዳዊት አማካይነት መከራ እንዲመጣባቸው አደረገ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን “ሄደህ የእስራኤልንና የይሁዳን ሕዝብ ቊጠር!” አለው፤ 2 ስለዚህም ዳዊት የጦሩ አዛዥ የሆነውን ኢዮአብን “የጦር መኰንኖችህን በማስከተል ከአገሪቱ ዳር እስከ ዳር ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ወዳሉት የእስራኤል ነገዶች ሁሉ ሄደህ ሕዝቡን ቊጠር፤ ምን ያኽል ሕዝብ እንዳለ ማወቅ እፈልጋለሁ” ሲል አዘዘው። 3 ኢዮአብ ግን “ንጉሥ ሆይ! አምላክህ እግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ አሁን ካሉት ይልቅ በመቶ እጅ ያብዛልህ፤ ይህንንም ሲያደርግ ለማየት እንድትበቃ ዕድሜህን ያርዝምልህ፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ! ይህን ለማድረግ ስለምን ፈለግኽ?” አለው፤ 4 ንጉሡ ግን ኢዮአብና የጦር መኰንኖቹ ትእዛዙን እንዲፈጽሙ ስላስገደዳቸው ከፊቱ ወጥተው የእስራኤልን ሕዝብ ለመቊጠር ሄዱ። 5 ዮርዳኖስንም ተሻግረው በጋድ ውስጥ በሚገኘው ሸለቆ መካከል ባለችው በዓሮዔር ከተማ በስተ ደቡብ ሰፈሩ፤ ከዚያም ወደ ሰሜን አምርተው ወደ ያዕዜር ደረሱ፤ 6 ቀጥለውም ወደ ገለዓድና በሒታውያን ግዛት ውስጥ ወዳለው ወደ ቃዴስ ዘለቁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ዳን፥ ከዳንም ወደ ምዕራብ ታጥፈው ወደ ሲዶና ሄዱ፤ 7 ቀጥሎም በደቡብ በኩል ወደተመሸገችው ወደ ጢሮስ ከተማና እንዲሁም ወደ ሒዋውያንና ወደ ከነዓናውያን ከተሞች ሁሉ ሄዱ፤ በመጨረሻም በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ቤርሳቤህ ዘለቁ፤ 8 በዚህ ዐይነት በመላ ሀገሪቱ ሲዘዋወሩ ቈይተው ዘጠኝ ወር ከኻያ ቀን ከሆናቸው በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 9 ኢዮአብም በእስራኤል ስምንት መቶ ሺህ፥ በይሁዳ አምስት መቶ ሺህ በውትድርና ለማገልገል ብቃት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውንም ለንጉሡ አሳወቀ። 10 ነገር ግን ዳዊት ሕዝቡን ከቈጠረ በኋላ የኅሊና ወቀሳ ስላስጨነቀው እግዚአብሔርን “እኔ ይህን በማድረጌ ታላቅ በደል ፈጽሜአለሁ፤ የሞኝነት ሥራ ስለ ሠራሁም እባክህ ይቅር በለኝ!” ሲል ለመነ። 11-12 እግዚአብሔርም የዳዊትን ነቢይ ጋድን “ሄደህ ዳዊትን ‘እነሆ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ እኔም አንተ የምትመርጠውን አደርግብሃለሁ’ ይላል” ብለህ ንገረው። በማግስቱ ጠዋት ዳዊት ከእንቅልፉ ከተነሣ በኋላ፥ 13 ጋድ ወዶ እርሱ ቀርቦ እግዚአብሔር ስለ እርሱ ያለውን ነገረው፤ ቀጠል አድርጎም “በምድርህ ሦስት ዓመት ራብ ከሚሆን፥ ለሦስት ወር ጠላቶችህ ከሚያሳድዱህና በምድርህ ላይ ለሦስት ቀን የቸነፈር መቅሠፍት ከሚሆን የትኛውን ትመርጣለህ? እንግዲህ በብርቱ አስብበትና ወደ እግዚአብሔር የማቀርበውን መልስ ስጠኝ” ሲል ጠየቀው። 14 ዳዊትም “እነሆ እኔ ለምርጫ በሚያስቸግር ሁኔታ ላይ ነኝ! ይሁን እንጂ በሰው እጅ መውደቅ አልፈልግም፤ እግዚአብሔር መሐሪ ስለ ሆነ እርሱ ራሱ ይቅጣኝ!” አለ። 15 ስለዚህ እግዚአብሔር ከዚያን ጠዋት ጀምሮ እስከ ወሰነው ቀን ድረስ በእስራኤል ላይ ቸነፈር አመጣ፤ በሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ማለትም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሰባ ሺህ እስራኤላውያን አለቁ። 16 የእግዚአብሔር መልአክ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ በሚዘጋጅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ መቅጣት ያለውን ውሳኔ ለውጦ ይቀሥፋቸው የነበረውን መልአክ “በቃህ! አቁም!” አለው፤ በዚህም ጊዜ መልአኩ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ላይ ቆሞ ነበር። 17 ዳዊትም ሕዝቡን ይቀሥፍ የነበረውን መልአክ አይቶ እግዚአብሔርን “በደል የፈጸምኩት እኔ ነኝ፤ እኔም ራሴ ክፉ ነገርን አደረግሁ፤ ታዲያ ይህ ምስኪን ሕዝብ ምን በደለህ? ይህ መቅሠፍት በእርሱ ላይ ከሚወርድ ይልቅ በእኔና በቤተሰቤ ላይ ይሁን” ሲል ጠየቀ። የዳዊት መሠዊያ መሥራት 18 በዚያው ዕለት ነቢዩ ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ “ወደ ኦርና አውድማ ሄደህ ለእግዚአብሔር መሠዊያውን ሥራ!” አለው፤ 19 ዳዊትም ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ጋድ እንደ ነገረው አደረገ፤ 20 ኦርናም ወደ ታች ሲመለከት ንጉሥ ዳዊትና ባለሟሎቹ የሆኑት ባለሥልጣኖች ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፤ እርሱም በዳዊት ፊት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ፤ 21 “ንጉሥ ሆይ! ስለምን ወደዚህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ዳዊትም “እግዚአብሔር የቸነፈሩን መቅሠፍት እንዲመልስ የአንተን አውድማ ለመግዛትና በዚያውም ላይ መሠዊያ ለመሥራት ነው የመጣሁት” አለው። 22 ኦርናም “ንጉሥ ሆይ! አውድማውን ወስደህ በፈቀድከው ዐይነት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርብበት፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ይቀርቡ ዘንድ እነሆ እነዚህ በሬዎች አሉ፤ ስለ ማገዶም ጉዳይ እነርሱ የሚጠመዱበት ቀንበርና የእህል መውቂያው እንጨት ሁሉ አለ” አለው። 23 ኦርናም “ይህን ሁሉ ለንጉሡ ሰጥቶ እግዚአብሔር መሥዋዕትህን ይቀበልልህ” አለው። 24 ንጉሥ ዳዊት ግን “ይህስ አይሆንም፤ ዋጋውን መክፈል አለብኝ፤ እኔ ምንም ዋጋ ያላወጣሁበትን ነገር ለአምላኬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጌ ማቅረብ አይገባኝም” አለው፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት አውድማውንና በሬዎቹን በኀምሳ ጥሬ ብር ገዛ፤ 25 ለእግዚአብሔርም መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት ሁሉ አቀረበ፤ እግዚአብሔርም የዳዊትን ጸሎት ሰማ፤ በእስራኤል ላይ የወረደውም የቸነፈር መቅሠፍት ከዚህ በኋላ ቆመ። |