Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ሴዴቅያስ የተነገረ የትንቢት ቃል

1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በግዛቱ ሥር ባሉት መንግሥታትና ሕዝቦች ጭምር እየተረዳ በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ላይ የጦርነት አደጋ በሚጥልበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።

2 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ወደ ይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዘንድ ሄጄ እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፤ “እኔ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ለባቢሎን ንጉሥ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።

3 አንተም ማምለጥ አትችልም፤ ትማረካለህ፤ ለእርሱም ተላልፈህ ትሰጣለህ፤ እርሱን በቀጥታ ፊት ለፊት ታየዋለህ፤ እርሱም ያነጋግርሃል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ባቢሎን ትሄዳለህ፤

4 ሴዴቅያስ ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ የምለውን ስማ፤ በጦርነት ላይ አትሞትም፤

5 በሰላም ታርፋለህ፤ ከአንተ በፊት ነገሥታት የነበሩ የቀድሞ አባቶችህ በሞቱ ጊዜ ሕዝቡ ለክብራቸው እሳት ያነዱላቸው እንደ ነበር ለአንተም እንዲሁ እሳት ያነዱልሃል፤ ‘ወዮ ንጉሣችን፥’ እያሉም ያለቅሱልሃል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

6 ይህንንም የትንቢት ቃል ለሴዴቅያስ በኢየሩሳሌም በነገርኩት ጊዜ፥

7 የባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት በኢየሩሳሌም ከዚያም አልፎ ላኪሽና ዐዜቃ ተብለው በሚጠሩት፥ በይሁዳ ቀርተው በነበሩት የመጨረሻ የተመሸጉ ከተሞች ላይ አደጋ እየጣለ ነበር።


የባሪያ ነጻነት

8 የባሪያ ነጻነትን ለማወጅ ሴዴቅያስ ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ጋር ተሰብስቦ ስምምነት ካደረገ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ ወደ ኤርምያስ መጣ።

9 ይኸውም ዕብራውያን ባሪያዎቻቸውን በሙሉ ሴቶችንም ወንዶችንም ነጻ ለማውጣት ነበር፤ ማንም ሰው እስራኤላውያን ከሆኑት ወገኖቹ መካከል ባሪያ እንዳይኖረው ወሰኑ።

10 ሕዝቡና መሪዎቻቸው ሁሉ ባሪያዎቻቸውን ነጻ ለመልቀቅና እንደገና መልሰውም ባሪያዎች ላለማድረግ ተስማሙ፤ በዚህም ስምምነት መሠረት ሁሉንም ነጻ አወጡአቸው፤

11 ዘግየት ብሎ ግን ሐሳባቸውን ለወጡና በባርነት ያገለገሉአቸው ዘንድ እንደገና ማስገደድ ጀመሩ።

12 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ፤

13 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ራሴ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር፥ ከባርነት ቤት ነጻ ባወጣኋቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲህ ስል ቃል ኪዳን ገብቼ ነበር።

14 በዚያም ቃል ኪዳን መሠረት፥ ዕብራውያን ባሪያዎች ያሉአቸው ሁሉ ስድስት ዓመት ካገለገሉአቸው በኋላ በሰባተኛው ዓመት ነጻ እንዲያወጡአቸው አዘዝኩ፤ ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችሁ ሊታዘዙኝም ሆነ ቃሌን ሊሰሙ አልፈለጉም፤

15 እነሆ እናንተም ከጥቂት ቀኖች በፊት ተጸጸታችሁ እኔን ደስ የሚያሰኝ ነገር መሥራት ጀምራችሁ ነበር፤ ሁላችሁም ከእስራኤላውያን ወገን የሆኑ ባሪያዎቻችሁን ነጻ ለመልቀቅ ተስማማችሁ፤ እኔ በምመለክበትም ቤተ መቅደስ ተሰብስባችሁ በፊቴ ቃል ኪዳን ገባችሁ፤

16 ነገር ግን እንደገና ሐሳባችሁን በመለወጥ ስሜን የሚያስነቅፍ ሥራ ሠራችሁ፤ ይኸውም ሁላችሁም እንደየፍላጎታቸው ነጻ የለቀቃችኋቸውን እንደገና ባሪያዎች አድርጋችሁ መግዛት ቀጠላችሁ።

17 እነሆ እኔ እግዚአብሔር እናንተንም የምላችሁ ይህ ነው፦ ‘አልታዘዛችሁም፤ ወገኖቻችሁ ለሆኑ እስራኤላውያንም ነጻነት አልሰጣችሁም፤’ ስለዚህም እኔ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ ትሞቱ ዘንድ እተዋችኋለሁ፤ በእናንተ ላይ በማደርገውም ነገር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲሠቀቅ አደርጋለሁ።

18 ባሪያዎቻችሁን ነጻ ለማውጣት በፊቴ ቃል ኪዳን በገባችሁ ጊዜ አንድን ጥጃ በመቊረጥ ለሁለት ከፍላችሁ በመካከሉ አልፋችኋል፤ ነገር ግን እናንተ ያን ቃል ኪዳንና እኔም ከእስራኤል ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አፍርሳችኋል፤ ስለዚህ እናንተ በጥጃው ላይ እንዳደረጋችሁት እኔ በእናንተ ላይ አደርጋለሁ።

19 የይሁዳና የኢየሩሳሌምን ታላላቅ ሰዎች፥ የቤተ መንግሥቱን ባለሥልጣኖች፥ ካህናቱንና ተቈርጦ በተከፈለው ጥጃ ብልቶች መካከል ያለፉትን የአገሪቱን ሕዝብ ሁሉ፥

20 ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚፈልጉ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ሬሳቸውንም ሁሉ የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊት ይበሉታል።

21 “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና መኳንንቱን ሁሉ ሕይወታቸውን ማጥፋት ለሚፈልጉ ጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሳልፌ የምሰጣችሁም በእናንተ ላይ አደጋ የመጣል ተግባሩን ለገታው ለባቢሎናውያን ሠራዊት ነው።

22 “እኔ ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ወደዚህች ከተማ ይመለሳሉ፤ አደጋ ጥለውም በመያዝ ያቃጥሉአታል፤ በይሁዳ የሚገኙ ከተሞችንም ሁሉ ማንም እንደማይኖርበት ባድማ አደርጋቸዋለሁ። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos