ኢሳይያስ 14:1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ግን ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፤ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይተሳሰራል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤ እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤ በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል። መጻተኞች ዐብረዋቸው ይኖራሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋራ ይተባበራሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእስራኤል እንደገና ምሕረትን ያደርጋል፤ የራሱ ወገኖችም አድርጎ ይመርጣቸዋል፤ እንደገናም በአገራቸው እንዲኖሩ ይፈቅድላቸዋል፤ መጻተኞችም እንኳ መጥተው ከእነርሱ ጋር ተስማምተው አብረው ይኖራሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፤ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፤ በሀገራቸውም ያርፋሉ፤ መጻተኞችም ከእነርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጨመራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፥ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል። |
በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከንዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዷ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።
ጌታ እንዲህ ይላል፦ የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።
አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ ከዚህ በኋላ ቅንጡና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ።
በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ የተወለደው ሕጻን ልጇን ትረሳለች? ርህራሄ አልባስ እስክመሆን ትደርሳለች? አዎን፥ እርሷ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።
ጌታ ግን እንዲህ ይላል፦ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁና፥ በኃያላን የተማረኩ እንኳን ይወሰዳሉ፥ የጨካኞች ብዝበዛም ቢሆን ያመልጣል።
የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ ጌታ፥ ሰዎች በሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው፥ ለገዢዎች አገልጋይ እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ ታማኙ ስለ ጌታ ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ።’
የአስጨናቂዎችሽ ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የጌታም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።
የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ ጌታ ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለጌታ ቁርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል ጌታ።
ነገር ግን፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር ካሳደዳቸውም ምድር ሁሉ ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
ከእናንተም ዘንድ ታገኙኛላችሁ፥ ይላል ጌታ፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተንም ለምርኮ ካፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
“በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ባዕዳን አገልጋይ አያደርጉህም፤
የእስራኤል ድንግል ሆይ! እንደገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ሐሤት በሚያደርጉ ዘፋኞች ሽብሸባ እያሸበሸብሽ ትወጫለሽ።
የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ልጆችና የይሁዳ ልጆች በአንድነት ተጨቊነዋል፥ የማረኳቸውም ሁሉ በኃይል ይዘዋቸዋል፥ እነርሱንም ለመልቀቅ እንቢ ብለዋል።
ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆች ለወለዱ ስደተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።
ደግሞም እንዲህም ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ እንደገና በብልጽግና ይሞላሉ፤ ጌታም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ምርጫው ያደርጋታል።
“ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፤ በሁሉም ስፍራ ለስሜ ዕጣን ያመጣሉ፥ ንጹሕ ቁርባንም ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል ታላቅ ይሆናል፥” ይላል የሠራዊት ጌታ።