Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 19 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት። እነሆ፥ ጌታ በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፤ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።

2 ግብፃውያንን በግብፃውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድም ወንድሙን፥ ባልንጀራም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።

3 የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን፥ የሙታን መናፍስትን፥ መናፍስት ጠሪዎቻቸውንና የጠንቋዮቻቸውን ምክር ይጠይቃሉ።

4 ግብጻውያንንም ለጨካኝ ገዢዎች አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል፥ ይላል ልዑል የሠራዊት ጌታ።

5 የዐባይ ወንዝ ይጎድላል፤ ወንዙም እያነሰም ይሄዳል ደረቅም ይሆናል።

6 መስኖዎቹም ይከረፋሉ፥ የግብጽም ጅረቶች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል።

7 በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ፥ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፤ ይበተናል፤ ምንም አይቀርም።

8 ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፤ በዐባይ ወንዝ ላይ መንጠቆአቸውን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፤ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት በድካም ይዝላሉ።

9 የተነደፈ የተልባ እግር ለሚፈትሉ፥ የተባዘተ ጥጥ የሚሰሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቆርጣሉ።

10 ሸማኔዎችዋም ሁሉ ቅስማቸው ይሰበራል፥ የደመወዘኞችም ልብ ይሰበራል።

11 የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሞኞች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው እርባና ቢስ ይሆናል። ፈርዖንን “እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን” እንዴት ትሉታላችሁ?

12 አሁንስ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ።

13 የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤ የሜምፎስም አለቆች ተታለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑት ግብጽን አስተዋታል።

14 ጌታ ግራ የመጋባት መንፈስ በውስጥዋ አፍሶባታል፤ ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ እንድትንገዳገድ አደረጓት።

15 ራስ ይሁን ጅራት፥ የዘንባባ ዝንጣፊ ይሁን ደንገል፥ ለግብጽ አንዳች ነገር ሊያደርጉላት አይችሉም።

16 በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ የተነሣ ይርዳሉ ይፈራሉም።

17 የይሁዳም ምድር ለግብጽ ሽብር ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል።

18 በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከንዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዷ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።

19 በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለጌታ መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ለጌታ ዓምድ ይቆማል።

20 ይህም ለሠራዊት ጌታ በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው ምክንያት ወደ ጌታ በመጮኻቸው፥ እርሱ መድኃኒትንና ኃያልን ሰዶ ያድናቸዋል።

21 በዚያም ቀን ጌታ ለግብጻዊያን ራሱን ይገልጣል፤ ግብጻውያንም ጌታን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በእህል ቁርባንም ያመልኩታል፤ ለጌታም ስእለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽማሉ።

22 ጌታም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ ጌታም ይመለሳሉ፥ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።

23 በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራዊያንም ወደ ግብጽ፥ ግብፃዊውም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብፃውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ።

24 በዚያ ቀን እስራኤል፤ ከግብጽና ከአሦር ጋር የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች።

25 የሠራዊት ጌታ፥ “ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos