Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 60 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የተበተኑት መሰብሰብ

1 ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የጌታም ክብር ወጥቶልሻልና ተነሺ፥ አብሪ።

2 እነሆ፥ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ ጌታ ይወጣል ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤

3 አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ፥ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።

4 ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሟቸዋል።

5 በዚያን ጊዜ የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ፥ የአሕዛብም ብልጽግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ፥ አይተሽ ደስ ይልሻል፥ ልብሽም ይደነቃል ይሰፋማል።

6 የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል፤ ከከሳባ የሆኑት ሁሉ ይመጣሉ፤ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ፥ የጌታን ምስጋና ያወራሉ።

7 የቄዳር መንጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነባዮትም አውራ በጎች ያገለግሉሻል፤ እኔን ደስ ሊያሰኙ በመሠዊያዬ ላይ ይወጣሉ፥ የክብሬንም ቤት አከብራለሁ።

8 ርግቦች ወደ ጎጇቸው እንደሚበርሩ፥ እነዚህ እንደ ደመና የሚበርሩ እነማን ናቸው?

9 እርሱ አክብሮሻልና ለአምላክሽ ለጌታ ስምና ለእስራኤል ቅዱስ ልጆችሽን ከሩቅ፥ ከእነርሱ ጋርም ብራቸውንና ወርቃቸውን ለማምጣት፥ ደሴቶች የተርሴስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል።

10 በቁጣዬ ቀሥፌ በፍቅሬ ምሬሻለሁና ባዕዳን ቅጥርሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ያገለግሉሻል።

11 በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጽግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ለማምጣት ሌሊትና ቀን አይዘጉም።

12 ለአንቺም የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፥ እነዚያ አሕዛብም ፈጽመው ይጠፋሉ።

13 የመቅደሴንም ስፍራ ለማስጌጥ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው፥ ባርሰነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ።

14 የአስጨናቂዎችሽ ልጆች አንገታቸውን ደፍተው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የጌታም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።

15 ከሰውም ማንም እስከማያልፍብሽ ድረስ የተተውሽና የተጠላሽ ነበርሽ፤ ነገር ግን የዘለዓለም ትምክሕትና የልጅ ልጅ ደስታ አደርግሻለሁ።

16 የአሕዛብንም ወተት ትጠጫልሽ፥ የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤ እኔም ጌታ፥ የያዕቆብ ኃያል፥ መድኃኒትሽና ታዳጊሽ እንደሆንሁ ታውቂያለሽ።

17 በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፥ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ፤

18 ከዚያ በኋላ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጉስቁልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥርሽን መዳን በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያለሽ።

19 ከዚያ በኋላ ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽም ይሆናልና በቀን ብርሃንሽ ፀሐይ መሆኑ ይቀራል፤ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያስፈልግሽም።

20 ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ታልቃለችና ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም፥ ጨረቃሽም አትገባም።

21 ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ እኔም እንድከብር የአታክልቴን ቡቃያ፥ የእጄ ሥራ የምትሆን ምድሪቱንም ለዘለዓለም ይወርሳሉ።

22 ታናሹ ለሺህ፥ የሁሉም ታናሹ ኃያል መንግሥት ይሆናል፤ እኔ ጌታ በዘመኑ ይህን በፍጥነት አደርገዋለሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos