Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 47 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ከመቅደሱ የሚፈልቀው ውሃ

1 ወደ ቤቱ መግቢያ መለሰኝ፤ እነሆ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር።

2 በሰሜኑ በር በኩል አወጣኝ፤ በውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በውጭ ወዳለው በር አመጣኝ፤ እነሆ ውኃው በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር።

3 ሰውዬው ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ፥ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ቁርጫምጭሚት ድረስ ነበር።

4 እንደገና አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ጉልበት ድረስ ነበር። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ድረስ ነበር።

5 ደግሞም አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።

6 እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? መራኝ፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ።

7 በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ።

8 እንዲህም አለኝ፦ ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ አውራጃ ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል።

9 ወንዙ በሚገባበት ስፍራ ያለ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ ይህ ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ የባሕሩ ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙ በሚገባበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።

10 ከዔንጌዲ ጀምሮ እስከ ዔንዔግላይም ድረስ አጥማጆች በዚያ ይቆማሉ፤ የመረቦች መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ።

11 ረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን አይፈወስም፤ ጨው እንደሆነ ይኖራል።

12 በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉ አይረግፍም ፍሬውም አያልቅም፤ ውኃው ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኩር ያፈራል፤ ፍሬው ለመብል ቅጠሉም ለፈውስ ይሆናል።


አዳዲስ የምድሪቱ ወሰኖች

13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ርስት አድርጋችሁ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት ድርሻ ይሆናል።

14 እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት፤ ለአባቶቻችሁ ልሰጣቸው ምዬ ነበር፥ ይህች ምድር በርስትነት ለእናንተ ሆናለች።

15 የምድሪቱ ድንበር ይህ ነው፤ በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጼዳድ መግቢያ፥

16 ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን፥

17 ድንበሩ ከባሕሩ ጀምሮ እስከ የደማስቆ ድንበር ሰሜን የሆነው ሐጻርዔኖን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። ይህም የሰሜኑ ድንበር ነው።

18 የምሥራቁ ድንበር በሐውራንና በደማስቆ፤ በገለዓድና በእስራኤልም ምድር መካከል እስከ ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ፤ ይህም የምሥራቁ ድንበር ነው።

19 የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ፥ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ይህም የደቡቡ ድንበር ነው።

20 የምዕራቡ ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። ይህም የምዕራቡ ድንበር ነው።

21 ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ትከፋፈላላችሁ።

22 ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆች ለወለዱ ስደተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።

23 ስደተኛው በተቀመጠበት ነገድ በዚያ ርስቱን ስጡት፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos