ኢሳይያስ 66 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድነው? 2 እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለች፤ እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል ጌታ። ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። 3 በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቁርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው። እጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል፤ 4 እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ። ምክንያቱም በፊቴ ክፉ ነገርን አድርገዋል፥ ያልወደድሁትንም መርጠው በጠራኋቸው ጊዜ አልመለሱልኝም፤ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝም። 5 እናንት በቃሉ ፊት የምትርዱ፥ የጌታን ቃል ስሙ፦ የጠሉአችሁ የናንተው ሕዝብ፥ ስለ ስሜም ያባረሩአችሁ፦ “ደስታችሁን እንድናይ ጌታ ይክበር” ብለዋል፤ ነገር ግን ያፍራሉ። 6 የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹ ላይ ፍዳን የሚያመጣ የጌታ ድምፅ ተሰምቶአል። 7 ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያስጭንቃት ወንድ ልጅን ወለደች። 8 ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳል? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። 9 በውኑ ወደ መውለድ የማደርስ እኔ እንዳይወለድ አደርጋለሁን? ይላል ጌታ፤ ሊወልድ የተቃረበውን ማኅፀንን እኔ እዘጋለሁን? ይላል አምላክሽ። 10 እናንተ የምትወዷት ሁሉ፥ ከኢየሩሳሌም ጋር ሐሤትን አድርጉ፤ ስለ እርሷም ደስ ይበላችሁ፤ እናንተም የምታለቅሱላት ሁሉ፥ ከእርሷ ጋር በደስታ ሐሤትን አድርጉ፤ 11 እንድትጠቡ ከማጽናናትዋም ጡት እንድትጠግቡ፥ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ እንዲላችሁ። 12 ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆም፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ከዚያም ትጠባላችሁ፥ በጫንቃ ላይ ይሸከሙአችኋል በጉልበትም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏችኋል። 13 እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። 14 ታያላችሁ፥ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፥ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የጌታም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፥ በጠላቶቹም ላይ ይቈጣል። 15 እነሆ፥ ጌታ መዓቱን በቁጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ ከእሳት ጋር ይመጣል፥ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። 16 ጌታም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፉ ይፈርዳል፤ በጌታም ተወግተው የሞቱት ይበዛሉ። 17 በመሀከላቸው ያለውን አንዱን ተከትለው ወደ መናፈሻ ስፍራው ለመግባት ሰውነታቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፥ የእሪያንም ሥጋ፥ አስጸያፊ ነገርንም፥ አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ። 18 ሥራቸውንና አሳባቸውን አውቃለሁ፤ አሕዛብንና ልሣናትን ሁሉ የምትሰበስብበት ጊዜ ይደርሳል፤ እነርሱም ይመጣሉ፥ ክብሬንም ያያሉ። 19 በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፥ ከእነርሱም የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ያዋን፥ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬንም ይናገራሉ። 20 የእስራኤል ልጆች ቁርባናቸውን በጥሩ ዕቃ አድርገው ወደ ጌታ ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁም ለጌታ ቁርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎች በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል ጌታ። 21 ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል ጌታ። 22 እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ከፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል ጌታ። 23 እንዲህ ይሆናል፤ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ለመስገድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል ጌታ። 24 ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ። |