ኤርምያስ 30 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለእስራኤልና ለይሁዳ የመታደስ ቃል ኪዳን 1 ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 “የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ የነገርሁህን ቃላት ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ። 3 እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል ጌታ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱአታል፥ ይላል ጌታ።” 4 ጌታ ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገራቸው ቃላት እነዚህ ናቸው። 5 ጌታ እንዲህ ይላልና፦ የሽብር ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም። 6 ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደሆነ ተመልከቱ፤ ስለምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ ሴት እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ገርጥቶ አየሁ? 7 ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል። 8 “በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ባዕዳን አገልጋይ አያደርጉህም፤ 9 ነገር ግን ጌታ አምላካቸውንና የማስነሣላቸውን ንጉሣቸውን ዳዊትን ያገለግላሉ። 10 “አንተ ባርያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ ይላል ጌታ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረኩበት አገር አድናለሁና፤ ያዕቆብም ይመለሳል ያርፋልም በደኅንነትም ይቀመጣል፤ እርሱንም ማንም አያስፈራራውም። 11 አንተን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል ጌታ፤ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ እንደጥፋትህ መጠን እቀጣሃለሁ እንጂ ያለ ቅጣት ከቶ አልተውህም። 12 “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስብራትህ የማይፈወስ ቁስልህም የማይሽር ነው። 13 ሙግትህን የሚፈርድልህ የለም፥ ለቁስልህም መድኃኒት የለውም፥ ለአንተም ፈውስ የለህም። 14 ውሽሞችህ ሁሉ ረስተውሃል አይፈልጉህምም፤ በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ ጨካኝ ሰው እንደሚቀጣው ጠላትም እንደሚያቆስለው አቁስዬሃለሁና። 15 ሕመምህ የማይፈወስ ነውና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ እነዚህን ነገሮች አድርጌብሃለሁ። 16 ስለዚህ የሚውጡህ ሁሉ ይዋጣሉ፥ ጠላቶችህም ሁሉ አንድም ሳይቀሩ ይማረካሉ፤ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፥ የበዘበዙህንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ። 17 ‘ማንም የማይሻት ጽዮን!’ ‘የተጣለች’ ብለው ጠርተውሻልና እኔ ጤናሽን እመልስልሻለሁ ቁስልሽንም እፈውሳለሁ፥ ይላል ጌታ። 18 “ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ዳግም ትሠራለች፥ የንጉሡ ቅጥርም ዱሮ በነበረበት ቦታ ላይ ይታነጻል። 19 ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች የሐሤት ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አስከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም። 20 ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፥ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ። 21 አለቃቸው ከእነርሱ ውስጥ አንዱ ይሆናል፥ ገዥአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፤ እኔ አቀርበዋለሁ እርሱም ይቀርበኛል፤ ይህስ ባይሆን ለነፍሱ ዋስትና ሰጥቶ ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል ጌታ። 22 እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።” 23 እነሆ፥ የጌታ ዐውሎ ነፋስ! ቁጣው ወጥቶአል፥ ጥቅል ዐውሎ ነፍስ፤ እርሱም በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። 24 የጌታ ጽኑ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ ይህን በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ። |