ሕዝቅኤል 25:13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኤዶምያስ ላይ እጄን እዘረጋለሁ፥ ከእርሷም ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማን ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ክንዴን በኤዶም ላይ አነሣለሁ፤ ሰዎቹንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማንም ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ አሁን ኤዶምን እንደምቀጣና በዚያም ያሉትን ሰዎችና እንስሶች በሙሉ እንደማጠፋ አሳውቃለሁ፤ ከቴማን ከተማ እስከ ደዳን ከተማ ድረስ ባድማ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ሕዝቡም በጦርነት ያልቃሉ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ ባድማም አደርጋታለሁ፤ ከቴማንና ከድዳንም ያመለጡ በሰይፍ ይወድቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፥ ከቴማንም ጀምሮ ባድማ አደርጋታለሁ፥ እስከ ድዳንም ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። |
በዚህ ምክንያት ጌታ፥ “ከምድር ላይ የፈጠርኩትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ሰው እና አራዊትን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን እና የሰማይ አእዋፍንም፥ ስለ ፈጠርኳቸው ተጸጽቼአለሁና” አለ።
ስለዚህ ጌታ በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ያሰባትን አሳብ ስሙ፤ በእውነት የመንጋው ትንንሾች እንኳ ይጐትቷቸዋል፤ በእውነት የማደሪያቸውም በረት በእነርሱ ላይ ይሣቀቃል።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቁጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይወርዳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።”
የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር ባለመታመን በእኔ ላይ ኃጢአት ብትሠራ፥ እጄን እዘረጋባታለሁ፥ የምግቧንም በትር እሰብራለሁ፥ ራብን እሰድድባታለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከእርሷ አጠፋለሁ፤
ፊቴን በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ፥ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቆርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር የቀሩትን አጠፋለሁ።
ስለዚህ እነሆ እጄን በአንተ ላይ ዘርግቻለሁ፥ እንዲበዘብዙህ ለሕዝቦች እሰጥሃለሁ፥ ከሕዝቦች እቆርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም እደመስስሃለሁ፤ አጠፋሃለሁም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃለህ።
ኤዶምያስ እና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኃይል የነበራችው በሰይፍ ከተገደሉት፥ ካልተገረዙት እና ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተኝተዋል።
እንዲህም በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሴይር ተራራ ሆይ፥ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ፥ እጄን እዘረጋብሃለሁ ባድማና ውድማም አደርግሃለሁ።
ሳባ፥ ድዳን፥ የተርሴስ ነጋዴዎች፥ መንገዶችዋም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን?