ሕዝቅኤል 25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በአሞን ላይ የተነገረ አዋጅ 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ አሞን ልጆች አድርገህ ትንቢት ተናገርባቸው። 3 ለአሞንም ልጆች እንዲህ በላቸው፦ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፥ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፥ የይሁዳም ቤት ተማርከው በተወሰዱ ጊዜ እሰይ ብለሻልና፤ 4 ስለዚህ እነሆ ርስት አድርጌ ለምሥራቅ ልጆች አሳልፌ እሰጥሻለሁ፥ እነርሱም በአንቺ ውስጥ ይሰፍራሉ፥ ማደሪያዎቻቸውንም በአንቺ ውስጥ ይሠራሉ፤ ፍሬሽን ይበላሉ ወተትሽንም ይጠጣሉ። 5 ራባን የግመሎች ማሰማርያ፥ የአሞንንም ልጆች ለመንጋ መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 6 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በእስራኤል ምድር ላይ በውስጥሽ ባለው ንቀት ሁሉ ደስ ብሎሽ በእጅሽ አጨብጭበሻልና፥ በእግርሽም አሸብሽበሻልና፥ 7 ስለዚህ እነሆ እጄን በአንተ ላይ ዘርግቻለሁ፥ እንዲበዘብዙህ ለሕዝቦች እሰጥሃለሁ፥ ከሕዝቦች እቆርጥሃለሁ፥ ከአገሮችም እደመስስሃለሁ፤ አጠፋሃለሁም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃለህ። በሞዓብ ላይ የተነገረ አዋጅ 8 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሞአብና ሴይር፦ እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎች ሕዝቦች ነው ብለዋልና፥ 9 ስለዚህ እነሆ የሞዓብን ጫንቃ ከከተሞቹ፥ በዳርቻው ካሉት የምድሩ ትምክሕት ከሆኑት ከተሞቹ፥ ከቤትየሺሞት፥ ከበኣልሜዎን፥ 10 ከአሞን ልጆች ጋር ለምሥራቅ ልጆች እከፍታለሁ። ከእንግዲህ ወዲህ የአሞን ልጆች በሕዝቦች መካከል እንዳይታሰቡ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ። 11 በሞዓብም ላይ ፍርድ እሰጣለሁ። እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። በኤዶም ላይ የተነገረ አዋጅ 12 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኤዶም በይሁዳ ቤት ላይ በቀል ተበቅሎአልና፥ በዚህም በደለኛ ሆኗል፥ በእነሱም ላይ ተበቅሎአልና፥ 13 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኤዶምያስ ላይ እጄን እዘረጋለሁ፥ ከእርሷም ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማን ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። 14 በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እንደ ቁጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ላይ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በፍልስጥኤማውያን ላይ የተነገረ አዋጅ 15 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ፍልስጥኤማውያን በቀልን አድርገዋልና፥ በዘወትርም ጠላትነት ያጠፉ ዘንድ በነፍሳቸው ንቀት ተበቅለዋልና 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እጄን በፍልስጥኤማውያን ላይ እዘረጋለሁ፥ ከሊታውያንንም እቆርጣለሁ፥ የባሕሩንም ዳር የቀሩትን አጠፋለሁ። 17 ቁጣ ከተሞላበት ቅጣት ጋር ታላቅ በቀል አደርግባቸዋለሁ፥ በቀሌን በእነሱ ላይ ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። |