Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


አብድዩ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 የአብድዩ ራእይ። ጌታ አምላክ ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከጌታ መልእክት ሰምተናል፥ መልእክተኛ ወደ አሕዛብ ተልኮ፦ ተነሡ፥ በላይዋም በጦርነት እንነሣ ብሏል።

2 እነሆ፥ በአሕዛብ ዘንድ ታናሽ አድርጌሃለሁ፥ አንተ እጅግ ተንቀሃል።

3 በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ የምትኖር፥ ማደሪያህንም ከፍ ከፍ ያደረግህ፥ በልብህም፦ ወደ ምድር የሚያወርደኝ ማን ነው? የምትል አንተ ሆይ፥ የልብህ ትዕቢት አታልሎሃል።

4 እንደ ንስር መጥቀህ ብትወጣ፥ ቤትህም በከዋክብት መካከል ቢሆን፥ ከዚያ አወርድሃለሁ፥ ይላል ጌታ።

5 ሌቦች ቢመጡብህ ወይም ወንበዴዎች በሌሊት ቢመጡ፥ የሚበቃቸውን ብቻ ይሰርቁ የለምን? ወይንንም የሚቆርጡ ወደ አንተ ቢመጡ ቃርሚያ ያስቀሩ የለምን? አንተ ግን ምንኛ ጠፋህ!

6 ዔሳው ምንኛ ተበረበረ! ብርቅዬ ሀብቱ ምንኛ ተፈለገ!

7 ከአንተ ጋር ቃል የተገባቡ ሰዎች ሁሉ ወደ ዳርቻህ ሰደዱህ፥ የታመንሃቸው ሰዎች አታለሉህ፥ አሸነፉህም፥ በበታችህም ወጥመድ ዘረጉብህ፥ እነርሱም ማስተዋል የላቸውም።

8 በዚያ ቀን ከኤዶምያስ ጥበበኞችን፥ ከዔሳውም ተራራ ማስተዋልን አላጠፋምን? ይላል ጌታ።

9 ቴማን ሆይ፥ ሰዎች ሁሉ ከዔሳው ተራራ በግድያ እንዲጠፉ ኃያላን ተዋጊዎችህ ይደነግጣሉ።

10 በወንድምህ በያዕቆብ ላይ ስለተደረገው ግፍ እፍረትን ትከናነባለህ፤ ለዘለዓለምም ትጠፋለህ።

11 በዳር ቆመህ በተመለከትክበት ቀን፥ አሕዛብ ሀብቱን በማረኩበት፥ ባእዳን በበሩ በገቡበት፥ በኢየሩሳሌምም ዕጣ በተጣጣሉበት ቀን አንተም እንደ እነርሱ ነበርህ።

12 ነገር ግን በወንድምህ የመከራ ቀን ልትደሰት፥ በጥፋታቸውም ቀን በይሁዳ ልጆች መጥፋት ደስ ሊልህ፥ በጭንቀታቸውም ቀን በትዕቢት ልትናገር አይገባም ነበር።

13 በጥፋታቸውም ቀን በሕዝቤ በር ልትገባ፥ በጥፋታቸውም ቀን መከራቸውን ልትመለከት፥ በጥፋታቸውም ቀን በሀብታቸው ላይ እጅህን ልትዘረጋ አይገባህም ነበር።

14 የሸሹትንም ለመግደል በመንታ መንገድ ላይ ልትቆም፥ በጭንቀትም ቀን ከእርሱ የቀሩትን አሳልፈህ ልትሰጥ አይገባህም ነበር።

15 የጌታ ቀን በአሕዛብ ሁሉ ላይ ቀርቧልና፥ አንተ እንዳደረግኸው እንዲሁ ይደረግብሃል፥ ፍዳህም በራስህ ላይ ይመለሳል።

16 በቅዱስ ተራራዬ ላይ እንደ ጠጣችሁ እንዲሁ አሕዛብ ሁሉ ዘወትር ይጠጣሉ፥ አዎን፥ ይጠጣሉ፥ ይጨልጡማል፥ እንዳልሆኑም ይሆናሉ።

17 ነገር ግን በጽዮን ተራራ ላይ የሚያመልጡ ይኖራሉ፥ እርሱም የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል፥ የያዕቆብም ቤት ሰዎች ርስታቸውን ይወርሳሉ።

18 ጌታ ተናግሮአልና የያዕቆብ ቤት እሳት፥ የዮሴፍ ቤት ነበልባልም፥ የዔሳው ቤት ገለባ ይሆናሉ፥ እነርሱንም ያቃጥሉአቸዋል ይበሉአቸውማል፥ ከዔሳውም ቤት የሚተርፍ አይኖርም።

19 የደቡብም ሰዎች የዔሳውን ተራራ፥ የቆላውም ሰዎች ፍልስጥዔማውያንን ይወርሳሉ፤ የኤፍሬምንም አገር የሰማርያንም አገር ይወርሳሉ፥ ብንያምም ገለዓድን ይወርሳል።

20 ይህም የእስራኤል ልጆች የጦር ምርኮ የከነዓንን ስፍራ ሁሉ እስከ ሰራጵታ ድረስ ይወርሳል፥ በስፋራድም የሚኖሩ የኢየሩሳሌም ምርኮኞች የደቡብን ከተሞች ይወርሳሉ።

21 በዔሳውም ተራራ ላይ ይፈርዱ ዘንድ አዳኞች ወደ ጽዮን ተራራ ላይ ይወጣሉ፥ መንግሥቱም ለጌታ ይሆናል።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos