ሕዝቅኤል 32 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሰቆቃ ስለ ፈርዖንና ስለ ግብጽ 1 እንዲህም ሆነ በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት በዓሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ሙሾ አውርድ፥ እንዲህም በለው፦ በሕዝቦች መካከል አንበሳ መሰልህ፥ እንደ ባሕር አውሬ ነበርህ፤ በወንዞችህም ገንፍለህ ወጥተሃል፥ ውኃውንም በእግርህ አደፍርሰሃል፥ ወንዞችህንም አሳድፈሃል። 3 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከብዙ ሕዝብ ጉባኤ ጋር ሆኜ መረቤን በላይህ ላይ እዘረጋለሁ፥ እነርሱም በመረቤ ያወጡሃል። 4 በምድር ላይ እተውሃለሁ፥ ለጥ ባለ ሜዳም እጥልሃለሁ፥ የሰማይ ወፎች ሁሉ በአንተ ላይ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፥ የምድርን አራዊት ሁሉ ከአንተ አጠግባቸዋለሁ። 5 ሥጋህን በተራሮች ላይ አደርጋለሁ፥ ሸለቆቹንም በሬሳህ ክምር እሞላለሁ። 6 የምትዋኝባትን ምድር እስከ ተራሮች ድረስ በደምህ አጠጣለሁ፥ መስኖዎች ከአንተ ይሞላሉ። 7 በማጠፋህ ጊዜ ሰማዮችን እሸፍናለሁ፥ ከዋክብቶቻቸውንም አጨልማለሁ፤ ፀሐይን በደመና እሸፍናለሁ፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም። 8 የሰማይን ብርሃኖች ሁሉ በአንተ ላይ አጨልማለሁ፥ በምድርህም ላይ ጨለማ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 በማታውቃቸውም አገሮች ባሉ በአሕዛብ ዘንድ ስብራትህን ባመጣሁ ጊዜ የብዙ ሕዝብን ልብ አስጨንቃለሁ። 10 ብዙም ሕዝቦች አንተን አይተው እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ ሰይፌንም በፊታቸው ባወዛወዝሁ ጊዜ ነገሥታቶቻቸው ይንቀጠቀጣሉ፤ በወደቅህበትም ቀን እያንዳንዱ ስለ ነፍሱ በየጊዜው ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። 11 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። 12 በኃያላን ሰይፍ ብዙ ሕዝብህን እጥላለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ጨካኞች ናቸው፤ የግበጽንም ትዕቢት ያወድማሉ ብዛትዋም ሁሉ ይጠፋል። 13 በብዙ ውኆች አጠገብ ያሉትን እንስሶች ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሰው እግር አያደፈርሰውም ወይም የእንስሳም ኮቴ አያደፈርሰውም። 14 በዚያን ጊዜ ውኆቻቸውን አጠራለሁ፥ ወንዞቻቸውም እንደ ዘይት እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 15 የግብጽንም ምድር ወና እና ባድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ ሞላዋንም ያጣች ምድር ባደረግኋት ጊዜ፥ የሚኖሩባትንም ሁሉ በመታሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንኩ ያውቃሉ። 16 የሚያወርዱት ሙሾ ይህ ነው፤ የአሕዛብ ቆነጃጅት፤ በግብጽና ብዛትዋ ሁሉ ላይ ሙሾን ያወርዳሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በግብጽ ላይ የወጣ ሙሾ 17 በዓሥራ ሁለተኛው ዓመት ከወሩም በዓሥራ አምስተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ግብጽ ብዛት ዋይ በል፥ እርሷንና የብርቱዎችን አሕዛብ ሴቶች ልጆች ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ታችኛው ምድር ጣላቸው። 19 በውበት የምትበልጪው ማን ነው? ውረጂ ካልተገረዙትም ጋር ተኚ። 20 በሰይፍ በተገደሉት መካከል ይወድቃሉ፤ ለሰይፍ ተሰጥታለች፤ እርሷንና ብዛትዋን ሁሉ ጐትቱ። 21 የኃያላን አለቆች በሲኦል ውስጥ ከረዳቶቹ ጋር ሆነው፤ ወደ ታች ወርደዋል በሰይፍም ከተገደሉት ካልተገረዙት ጋር ተኝተዋል፤ ይሏቸዋል። 22 አሦርና ጉባኤዋ ሁሉ በዚያ አሉ፤ በሰይፍ ወድቀው በተገደሉባት ሰዎች ሁሉ መቃብር ተከባለች። 23 መቃብራቸው በጥልቅ ጉድጓድ በውስጠኛው ክፍል ነው፥ ጉባኤዋም በመቃብሯ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸበሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል 24 ኤላምም በዚያ አለች ብዛትዋም ሁሉ በመቃብሯ ዙሪያ ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸበሩ ሁሉ በሰይፍ ወድቀው ተገድለዋል ሳይገረዙም ወደ ታችኛው ምድር ወርደዋል፥ ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። 25 በመቃብሯ ዙሪያ በተገደሉት መካከል ከብዛትዋ ሁሉ ጋር መኝታን አድርገውላታል፤ ሁሉም ያልተገረዙና በሰይፍ የተገደሉ ናቸው፤ በሕያዋንም ምድር ያሸብሩ ነበር ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱ ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል፥ በተገደሉትም መካከል ተሰጥተዋል። 26 ሜሼክና ቱባል ብዛታቸውም ሁሉ በዚያ አሉ መቃብራቸውም በዙሪያቸው ነው፤ በሕያዋን ምድር ያሸብሩ ስለ ነበር ሁሉም ያልተገረዙ ሲሆኑ በሰይፍ ተገድለዋል። 27 ከወደቁ ኃያላን ካልተገረዙ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው፥ ሰይፋቸውንም ከራስጌያቸው በታች አድርግው ወደ ሲኦል ከወረዱ ጋር አልተኙም፥ በሕያዋንም ምድር ያሸብሩ ስለ ነበር ኃጢአታቸውም በአጥንታቸው ላይ ነበር 28 አንተም ባልተገረዙት መካከል ትሰበራለህ፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ትተኛለህ። 29 ኤዶምያስ እና ነገሥታቶችዋ አለቆችዋም ሁሉ በዚያ አሉ፤ ኃይል የነበራችው በሰይፍ ከተገደሉት፥ ካልተገረዙት እና ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተኝተዋል። 30 የሰሜን አለቆች ሁሉ ሲዶናውያንም ሁሉ ከተገደሉት ጋር ወርደው በዚያ አሉ፤ በኃይላቸውም ያስፈሩ በነበረው ፍርሃት አፍረዋል፥ በሰይፍም ከተገደሉት ጋር ሳይገረዙ ተኝተዋል፥ ወደ ጉድጓድም ከሚወርዱት ጋር እፍረታቸውን ተሸክመዋል። 31 በሰይፍ የተገደሉ ፈርዖንና ሠራዊቱ ሁሉ ያዩአቸዋል ፈርዖንም ስለ ብዛቱ ሁሉ ይጽናናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 32 መፈራቱን በሕያዋን ምድር አድርጌአለሁ፥ ፈርዖንና ብዛቱም ሁሉ በሰይፍ በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ይተኛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |