ሕዝቅኤል 29 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)በግብጽ ላይ የወጣ አዋጅ 1 በአሥረኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር ከወሩም በዓሥራ ሁለተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፥ በእርሱና በግብጽ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤ 3 እንዲህም ብለህ ተናገር፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “‘ወንዙ የእኔ ነው እኔ ራሴ ሠርቼዋለሁ’ የምትል፥ በወንዞች መካከል የምትተኛ፥ አንተ ታላቅ ድራጎን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ፥ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ። 4 በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፥ የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤ በቅርፊትህ ከተጣበቁት የወንዞችህ ዓሦች ሁሉ ጋር ከወንዞችህ መካከል አወጣሃለሁ። 5 አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፤ በሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ አትከማችም፥ አትሰበሰብም፤ ምግብ እንድትሆን ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች እሰጥሃለሁ። 6 ለእስራኤል ቤት የመቃ በትር ሆነዋልና በግብጽ የሚኖሩ ሁሉ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 7 በእጅህ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ ትከሻቸውን ሁሉ ቆረጥህ፤ በአንተ ላይ ሲደገፉ ተሰበርህ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።” 8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሰይፍ አመጣብሻለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከአንቺ አጠፋለሁ። 9 የግብጽ ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ምክንያቱም ወንዙ የእኔ ነው፥ የሠራሁትም እኔ ነኝ ብሏልና። 10 ስለዚህ፥ እነሆ፥ በአንተ ላይ ነኝ፥ በወንዞችህም ላይ ነኝ፥ የግብጽን ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴቬኔና እስከ ኢትዮጵያ ጠረፍ ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ። 11 በእርሷ በኩል የሰው እግር አያልፍም፥ የእንስሳም እግር አያልፍም፥ ለአርባ ዓመትም ማንም አይኖርባትም። 12 የግብጽን ምድር ባድማ በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ አደርጋታለሁ፥ ከተሞችዋንም በፈረሱት ከተሞች መካከል ለአርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብጻውያንንም ወደ ሕዝቦች እበትናቸዋለሁ፥ በአገሮችም እዘራቸዋለሁ። 13 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አርባውም ዓመት ሲያልቅ ግብጻውያንን ከተበተኑባቸው ሕዝቦች መካከል እሰበስባለሁ፤ 14 የግብጽን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ወደ ተወለዱባት ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ። 15 ከመንግሥታት ሁሉ ይልቅ የተዋረደች ትሆናለች፤ ከእንግዲህ ወዲያ በሕዝቦች ላይ ከፍ ከፍ አትልም፤ በሕዝቦችም መካከል እንዳይገዙ አሳንሳቸዋለሁ። 16 ከእንግዲህ ወዲያ ለእስራኤል ቤት መታመኛ አይሆንም፥ እነርሱን በተከተሉ ጊዜ በደልን ያሳስባል፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ። ባቢሎን ግብጽን ትዘርፋለች 17 እንዲህም ሆነ በሀያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18 የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በጢሮስ ላይ ሠራዊቱን ጽኑ ሥራ አሠራ፤ ራስ ሁሉ ተመልጧል፥ ትከሻም ሁሉ ተልጦአል፥ ሆኖም በእርሷ ላይ ለሰሩት ሥራ እርሱም ሆነ ሠራዊቱ ከጢሮስ ደመወዝ አልተቀበሉም። 19 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብጽን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛትዋን ያነሳል፥ ምርኮዋን ይማርካል፥ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል። 20 ለእኔ ሠርተዋልና ለሠራው ሥራ ካሳ የግብጽን ምድር ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 21 በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፥ ለአንተ ደግሞ በመካከላቸው የተከፈተ አፍን እሰጥሃለሁ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። |