ሕዝቅኤል 27 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ስለ ጢሮስ የወጣ ሙሾ 1 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ስለ ጢሮስ ሙሾ አውርድ፥ 3 በባሕር መግቢያ ለምትኖረውና፥ በብዙ ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ለምትነግደው ጢሮስ እንዲህ በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ፥ አንቺ፦ “በውበት ፍጹም ነኝ” ብለሻል። 4 ዳርቻሽ በባሕር ልብ ነው፤ ሠሪዎችሽ ውበትሽን ፍጹም አደረጉ። 5 ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሴኒር በመጣ ጥድ ሠሩ፤ ደቀልንም ሊሰሩልሽ ከሊባኖስ ዝግባ ወሰዱ። 6 በባሻን ባሉጦች መቅዘፊያሽን ሠሩ፤ በዝሆን ጥርስ ከታሻበ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍ ወለልሽን ሠርተዋል። 7 ዓላማ ሆኖ እንዲያገለግልሽ፥ ሸራሽ ከግብጽ በፍታና ከወርቀ ዘቦ ተሠርቶአል፥ መደረቢያሽም ከኤሊሻ ደሴቶች የመጣ ሰማያዊና የወይን ጠጅ ነበር። 8 የሲዶናና የአርቫድ ነዋሪዎች ቀዛፊዎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የነበሩት ባለሙያዎችሽ የመርከቦችሽ መሪዎች ነበሩ። 9 በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው ከአንቺ ጋር ለመለዋወጥ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። 10 ፋርስ፥ ሉድና ፉጥ በሠራዊትሽ ውስጥ ወታደሮችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቁርም በአንቺ ውስጥ ሰቀሉ፤ ውበትን ሰጡሽ። 11 የአርቫድ ልጆችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ ዙሪያውን ነበሩ፥ ጋማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ ጋሻቸውንም በቅጥርሽ ዙሪያ ሰቀሉ፥ ውበትሽንም ፍጹም አደረጉ። 12 ከሀብትሽ ብዛት የተነሣ ተርሴስ ነጋዴሽ ነበረች፥ በብርና በብረት በቆርቆሮና በእርሳስ ዕቃሽን ለወጡ። 13 ያቫን፥ ቱባልና ሜሼክ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር፤ ዕቃሽን በሰዎች ነፍስና በናስ ዕቃ ይለውጡ ነበር። 14 የቶጋርማ ቤትም ዕቃዎችሽን በፈረሶች፥ በፈረሰኞችና በበቅሎዎች ለወጡ። 15 የድዳን ልጆችም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ይለውጡ ዘንድ የዝሆን ጥርስና ዞጲ አመጡልሽ። 16 ከምርትሽ ብዛት የተነሣ አራም ነጋዴሽ ነበረች፤ ዕቃዎችሽን በበሉር፥ በወይን ጠጅ፥ በወርቀ ዘቦ፥ በጥሩ በፍታም በዛጐልም በቀይ ዕንቁም ይቀይሩ ነበር። 17 ይሁዳና የእስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ዕቃዎችሽን በሚኒት ስንዴ፥ ጣፋጭ ዳቦ፥ ማር፥ ዘይትና በለሳን ይለውጡ ነበር። 18 በሁሉም ነገር ሀብታም ስለ ነበርሽ፥ ከንብረትሽ ብዛት የተነሣ፥ ደማስቆ በሔልቦን የወይን ጠጅ፥ ነጭ የበግ ጠጉር፥ ነጋዴሽ ነበረች። 19 ከኡዛል ቭዳንና ያቫን ዕቃዎችሽን ይለውጡ ነበር፤ የተሠራ ብረትና ብርጉድ ቀረፋም ሸቀጥሽ ነበረ። 20 ድዳን ለግልቢያ በሚሆን ኮርቻ ነጋዴሽ ነበረች። 21 ዓረብና የቄዳር ልዑላን ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በጠቦቶች፥ በአውራ በጎችና በፍየሎች በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 22 የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ምርጥ በሆኑ ቅመማ ቅመሞች ሁሉ፥ በክበረ ድንጋይ ሁሉና በወርቅ ሸቀጥሽን ይለውጡ ነበር። 23 ሐራን፥ ካኔ፥ ዔድን፥ የሳባ ነጋዴዎች፥ አሦርና ኪልማድ ነጋዴዎችሽ ነበሩ። 24 እነዚህ በገበያሽ ውስጥ በአማረ ልብስ፥ በሰማያዊ ካባ፥ በወርቀ ዘቦ፥ በዝግባ በተሠራች በገመድም በታሰረች በግምጃም በተሞላች ሳጥን ይነግዱ ነበር። 25 የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚያጓጉዙልሽ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር፥ በባሕርም ልብ ውስጥ እጅግ ከበርሽ። 26 ቀዛፊዎችሽ ወደ ታላቅ ውኆች አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ልብ ሰበረሽ። 27 ሀብትሽ፥ ሸቀጥሽ፥ ንግድሽ፥ መርከበኞችሽ፥ መርከብ መሪዎችሽ፥ ሰባራሽን የሚጠግኑ፥ ሸቀጥሽን የሚነግዱ፥ በአንቺ ውስጥ ያሉ ወታደሮችሽ ሁሉ፥ በውስጥሽ ካሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በውድቀትሽ ቀን ወደ ባሕር ልብ ይወድቃሉ። 28 ከመርከብ መሪዎች ጩኸት ድምፅ የተነሣ መሰማሪያዎች ይንቀጠቀጣሉ። 29 መቅዘፊያውን የያዙት ሁሉ፥ መርከበኞች፥ የባሕር መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ፤ በመሬትም ላይ ይቆማሉ፥ 30 ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፥ ምርር ብለው ይጮኻሉ፤ በራሳቸውም ላይ አቧራ ይነሰንሳሉ፤ በአመድም ላይ ይንከባበላሉ፤ 31 ስለ አንቺ ጠጉራቸውን ይላጫሉ፥ ማቅም ይታጠቃሉ፤ በነፍስ ምሬትም ስለ አንቺ መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ። 32 በልቅሶአቸውም ስለ አንቺ ሙሾን ያነሡልሻል፥ እንዲህም እያሉ በአንቺ ላይ ያሞሻሉ፦ በባሕር መካከል ጠፍቶ የቀረ እንደ ጢሮስ ማን ነው? 33 ሸቀጥሽ ከባሕር በወጣ ጊዜ ብዙ ሕዝቦችን አጥግበሻል፤ በተትረፈረፈ በሀብትሽና በሸቀጣ ሸቀጥሽ የምድርን ነገሥታት አበልጽገሻል። 34 በጥልቅ ውኆች ውስጥ፥ በባሕር በተሰበርሽ ጊዜ ግን ሸቀጣ ሸቀጥሽና በመካከልሽ ያሉ ጉባኤሽ ሁሉ ወድቀዋል። 35 በደሴቶች የሚኖሩ ሁሉ በአንቺ ደንግጠዋል፥ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል፥ ፊታቸውም ተለውጦአል። 36 ከሕዝቦች መካከል ያሉ ነጋዴዎች አፏጩብሽ፤ አስደንጋጭ ሆነሻል፥ ለዘለዓለምም አትገኚም። |