Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሕዝቅኤል 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የእግዚአብሔር ፍርድ ተገቢነት

1 ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አንዳንዶች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ።

2 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

3 የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፥ ታዲያ እንዲጠይቁኝ ልፍቀድላቸው?

4 ስለዚህ ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማንም ሰው ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ወደ ነቢዩም የሚመጣ፥ እኔ ጌታ እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ።

5 ይህም የእስራኤልን ቤት ለመያዝ ነው፤ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ምክንያት በልባቸው ከእኔ ተለይተዋልና፤

6 ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመለሱ፥ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ፊታችሁን መልሱ።

7 ማንም ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም የሚቀመጥ መጻተኛ፥ ራሱን ከእኔ የሚለይ፥ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ስለ እኔም ለመጠየቅ ወደ ነቢዩ የሚመጣ፥ እኔ ጌታ ራሴ እመልስለታለሁ፥

8 ፊቴን በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ፥ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

9 ነቢዩ ቢታለል፥ ቃልንም ቢናገር፥ ያንን ነቢይ ያታለልሁ እኔ ጌታ ነኝ፥ በእርሱም ላይ እጄን እዘረጋለሁ፥ ከሕዝቤ ከእስራኤል መካከልም አጠፋዋለሁ።

10 በደላቸውን ይሸከማሉ፥ እንደ ጠያቂው በደል የነቢዩም በደል እንዲሁ ይሆናል።

11 ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግመው ከእኔ ርቀው እንዳይጠፉ፥ በመተላለፋቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፥ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

12 የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

13 የሰው ልጅ ሆይ፥ ምድር ባለመታመን በእኔ ላይ ኃጢአት ብትሠራ፥ እጄን እዘረጋባታለሁ፥ የምግቧንም በትር እሰብራለሁ፥ ራብን እሰድድባታለሁ፥ ሰውንና እንስሳንም ከእርሷ አጠፋለሁ፤

14 ኖኅ ዳንኤልና ኢዮብ እነዚህ ሦስት ሰዎች፥ በውስጧ ቢኖሩ እንኳ በጽድቃቸው የገዛ ነፍሳቸውን ያድናሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15 ክፉ አውሬ በምድሪቱ እንዲያልፍ ባደርግ፥ ልጅ አልባ ቢያደርጋት፥ በአውሬው ምክንያት ማንም እንዳያልፍባት ባድማ ብትሆን፥

16 እነዚህ ሦስት ሰዎች በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም፥ ምድሪቱም ባድማ ትሆናለች።

17 ወይም በዚያች ምድር ላይ ሰይፍ አምጥቼ፦ በምድሪቱ ላይ ሰይፍ ይለፍ ብል፥ ሰውንና እንስሳን ከእርሷ ባጠፋ፥

18 እነዚህ ሦስት ሰዎች በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ እነርሱ ብቻቸውን ይድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።

19 ወይም በዚያች ምድር ላይ ቸነፈር ብሰድድ፥ ቁጣዬን በደም ባፈስስባትና ሰውንና እንስሳንም ከእርሷ ባጠፋ፥

20 ኖኅ፥ ዳንኤልና ኢዮብ በውስጧ ቢኖሩ፥ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በጽድቃቸው ነፍሳቸውን ያድናሉ እንጂ ወንዶችንና ሴቶች ልጆቻቸውን አያድኑም።

21 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ላይ አራቱን ክፉ ፍርዶቼን ሰይፍ፥ ራብ፥ ክፉ አውሬና ቸነፈር፥ ሰውንና እንስሳን ከእርሷ ለማጥፋት ብሰድድም፥

22 ነገር ግን እነሆ፥ የሚያመልጡና ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን የሚያወጡ ይቀሩላታል፥ እነሆ ወደ እናንተ ይመጣሉ፥ እናንተም መንገዳቸውንና ሥራቸውን ታያላችሁ፥ በኢየሩሳሌም ላይ ስላመጣሁት ክፉ ነገር፥ ስላመጣሁባትም ነገር ሁሉ ትጽናናላችሁ።

23 መንገዳቸውንና ሥራቸውን ባያችሁ ጊዜ ያጽናኑአችኋል፥ ያደረግሁትም ሁሉ በከንቱ እንዳላደረግሁት ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos