Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ነቢዩ ኤርምያስ የጌታን ፍርድ መናገሩ

1 ከጌታ ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።

2 “በጌታ ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል በዚያ እንዲህ ብለህ አውጅ፦ ጌታን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ሰዎች ሆይ! ሁላችሁ የጌታን ቃል ስሙ።

3 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ።

4 ‘የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ፥ የጌታ መቅደስ ይህ ነው’ እያላችሁ በእነዚህ የሐሰት ቃላት አትታመኑ።

5 መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥

6 መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትጨቊኑ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም እንዳይሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥

7 ከጥንት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር፥ በዚህ ስፍራ እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ።

8 “እነሆ፥ በማይረባ በሐሰት ቃላት ታምናችኋል።

9 ትሰርቃላችሁን፥ ትገድላላችሁን፥ ታመነዝራላችሁን፥ በሐሰትም ትምላላችሁን፥ ለበዓልም ታጥናላችሁን፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁን፤

10 መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ፦ እነዚህን አስጸያፊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማድረግ ‘እኛ ድነናል’ አላችሁ።

11 ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ ራሴ አይቻለሁ፥ ይላል ጌታ።”

12 ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ምን እንዳደረግሁበት እዩ።

13 አሁንም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ይላል ጌታ፥ በማለዳም ተነሥቼ ባለማቋረጥ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥

14 ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ።

15 የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።


የሕዝቡ አለመታዘዝ

16 “እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፤ አትማልድላቸው።

17 እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን?

18 እኔን ለማስቆጣት፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ፥ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ፤ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቁርባን ያፈስሳሉ።

19 እኔን ያስቈጣሉን? ይላል ጌታ፤ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን?

20 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቁጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይወርዳል፤ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።”

21 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በሌላ መሥዋዕቶቻችሁ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ።

22 ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም።

23 ነገር ግን፦ “ድምፄን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም እንዲሆንላችሁ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ” ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው።

24 ነገር ግን በክፉ ልባቸው ሐሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም።

25 አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሜ ላክሁባችሁ።

26 ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።

27 “ይህን ሁሉ ቃላት ለእነርሱ ትናገራለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም።”

28 አንተም፦ “የአምላኩን የጌታን ድምፅ ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ታጥቶአል።

29 ጌታ የቁጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጉርሽን ቁረጪ፥ ጣዪውም፥ በተራቈቱ ኮረብቶችም ላይ ሙሾን አውጪ፥” ትላቸዋለህ።

30 “የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል ጌታ፤ ሊያረክሱትም ስሜ በተጠራበትን ቤት ውስጥ ርኩሰታቸውን አኑረዋል።

31 እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ለማቃጠል፥ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያሉትን የቶፌት መስገጃዎችን ሠረተዋል።

32 ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከመታጣቱ የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ።

33 የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድርም አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም።

34 ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ አጠፋለሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos