ራእይ 11:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሁለቱ ምስክሮቼ የሐዘን ልብስ ለብሰው አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ኀይል እሰጣቸዋለሁ።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም ለሁለቱ ምስክሮቼ ኀይል እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ማቅ ለብሰው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ይናገራሉ።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት እንዲናገሩ ለሁለቱም ምስክሮቼ ኃይል እሰጣለሁ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። |
ከዚህ በኋላ ዳዊት በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው፥ ማቅ ለብሰው ለአበኔር እንዲያለቅሱ ኢዮአብንና የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች አዘዘ፤ በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ንጉሥ ዳዊት ራሱ አስክሬኑን ተከትሎ ሄደ፤
ኤልያስ ንግግሩን ከፈጸመ በኋላ አክዓብ ልብሱን በመቅደድና አውልቆ በመጣል ማቅ ለበሰ፤ እህል መቅመስንም እምቢ አለ፤ ማቁንም እንደ ለበሰ ይተኛ ነበር፤ ሲሄድም ከጭንቀቱ ብዛት የተነሣ ፊቱ ጠቊሮ ይታይ ነበር።
ዳዊትም መልአኩ ኢየሩሳሌምን ለመደምሰስ ሰይፉን በእጁ እንደ ያዘ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ አየው፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ማቅ ለብሰው የነበሩት የሕዝቡ አለቆች በሙሉ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ።
በዚሁ ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ስለ ኃጢአታቸው መጸጸታቸውንና ማዘናቸውን ለመግለጥም ማቅ ለብሰው፥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ጾሙ፤
የኢየሩሳሌም ከተማ ሽማግሌዎች ጸጥ ብለው በምድር ላይ ተቀመጡ፤ እነርሱ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ማቅ ለበሱ፤ የኢየሩሳሌም ልጃገረዶች አንገታቸውን ደፉ።
ያንንም ከፈጸምክ በኋላ ተዛውረህ በቀኝ ጐንህ በመተኛት እንደገና የይሁዳን በደል አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ ይህም እነርሱን በምቀጣበት በእያንዳንዱ ዓመት ልክ ይሆናል ማለት ነው።
ቀጭን ሐር ለብሶ ከወንዝ በላይ በኩል የቆመው መልአክ ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ በዘለዓለማዊው አምላክ ስም በመማል “ሦስት ዓመት ተኩል ይወስዳል፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሚደርሰው መከራ ሲያከትም እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተፈጻሚነት ያገኛሉ።”
በልዑል እግዚአብሔር ላይ በመታበይ ይናገራል፤ የልዑል እግዚአብሔርንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ የተቀደሱ በዓላትንና ሕጉን ለመለወጥ ያቅዳል፤ ቅዱሳኑም ለሦስት ዓመት ተኩል በእርሱ ሥልጣን ሥር ይሆናሉ።
የተጠየቀውም ቅዱስ “የጠዋትና የማታ መሥዋዕት የማይቀርብባቸው ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ቀኖች ይሆናሉ፤ ከዚያን በኋላ ቤተ መቅደሱ ይነጻል” ብሎ ሲመልስለት ሰማሁ።
ለአምላካችሁ የምታቀርቡት የእህልም ሆነ የወይን ጠጅ መባ ስለሌለ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች የሆናችሁ ካህናት! ኑና ማቅ ለብሳችሁ ሌሊቱን ሁሉ አልቅሱ! እናንተም በመሠዊያው ላይ የምታገለግሉ ዋይ! ዋይ! በሉ።
ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ።
“ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ በላያቸው ላይ ነስንሰው ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር!
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ ላይ ተቀምጠው፥ ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር።
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”
ስለዚህ እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው በቤተ ክርስቲያን የተለያየ አገልግሎት እንዲኖረው አድርጓል፤ በዚህም መሠረት በመጀመሪያ ሐዋርያትን፥ ሁለተኛ ነቢያትን፥ ሦስተኛ መምህራንን ሾሞአል። ቀጥሎም ተአምራት የሚያደርጉትን፥ ቀጥሎም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፥ ሰዎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፥ አስተዳዳሪዎችንና በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩትን ሰዎች መድቦአል።
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ አንዳንዶቹ ነቢያት፥ አንዳንዶቹ የወንጌል ሰባኪዎች፥ አንዳንዶቹ የምእመናን እረኞች፥ አንዳንዶቹ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ስጦታዎችን ሰጣቸው።
ሆኖም በዚህ ሁኔታ በሞት መቀጣት የሚገባው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በእርሱ ላይ ከመሰከሩበት በኋላ ነው፤ ምስክሩ አንድ ብቻ ከሆነ ግን ያ ሰው አይገደል።
“የአንድን ሰው ወንጀለኛነት ለማረጋገጥ አንድ ምስክር ብቻ አይበቃም፤ አንድ ሰው ወንጀለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ያስፈልጋሉ።
ከቤተ መቅደሱ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ ግን ተወው፤ እርሱ ለአሕዛብ የተሰጠ ስለ ሆነ አትለካው፤ አሕዛብ ቅድስቲቱን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ይረግጡአታል፤
እነርሱ ትንቢት በሚናገሩባቸው በእነዚህ ቀኖች ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ለመዝጋት ሥልጣን አላቸው፤ እንዲሁም ውሃዎችን ወደ ደም ለመለወጥና በሚፈልጉትም ጊዜ ሁሉ በማንኛውም ዐይነት መቅሠፍት ምድርን ለመምታት ሥልጣን አላቸው።
ሴቲቱም ወደ በረሓ ሸሽታ ሄደች፤ እዚያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን በእንክብካቤ ተይዛ የምትጠበቅበትን ስፍራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶላት ነበር።
እኔም ለመልአኩ ልሰግድለት በእግሩ ሥር በግንባሬ ተደፋሁ፤ እርሱ ግን “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክርነት ከያዙት ወንድሞችህ ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ! የኢየሱስ ምስክርነት የትንቢት መንፈስ ነው” አለኝ።
ከዚህ በኋላ ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ የመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ተቀምጠው አየሁ፤ ስለ ኢየሱስ በመመስከራቸውና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሶች አየሁ፤ እነርሱ ለአውሬውና ለምስሉ ያልሰገዱ፥ ምልክቱንም በግንባራቸውም ሆነ በእጃቸው ላይ ያላደረጉ ናቸው፤ እነርሱ ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ።