ኢዩኤል 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየአንበጣ መንጋ ያስከተለው ጥፋት 1 ለባቱኤል ልጅ ለኢዩኤል ከእግዚአብሔር የመጣለት የትንቢት ቃል ይህ ነው፦ 2 እናንተ ሽማግሌዎች ይህን ስሙ! በይሁዳም ምድር የምትኖሩ ሁሉ ይህን አድምጡ! ለመሆኑ ይህን የመሰለ ነገር በዘመናችሁ ወይም በቀድሞ አባቶቻችሁ ዘመን ተደርጎ ያውቃልን? 3 ይህን ነገር ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው ይንገሩ፤ እነርሱ ደግሞ ለሚከተለው ትውልድ ይንገሩ። 4 ከተምች መንጋ የተረፈውን ሰብል፥ የሚርመሰመስ የአንበጣ መንጋ በላው፤ ከዚያ የተረፈውን እንደ ውሽንፍር የሚገርፍ የአንበጣ መንጋ አጠፋው፤ ከዚያም የተረፈውን ኲብኲባ በላው። 5 ከእንግዲህ ወዲህ አዲስ የወይን ጠጅ በአፋችሁ ስለማትቀምሱ፥ እናንተ ሰካራሞች ከእንቅልፋችሁ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ መጠጣት የምታዘወትሩ ምርር ብላችሁ አልቅሱ። 6 ስፍር ቊጥር የሌለው የአንበጣ መንጋ፥ እንደ ወራሪ ጦር በምድሬ ላይ መጥቶአል፤ ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ ነው፤ መንጋጋውም እንደ ሴት አንበሳ መንጋጋ ነው። 7 የወይን ተክሎቼን ሁሉ አጠፋ፤ የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤ ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስከሚታዩ ድረስ፥ ቅርፊቱን ልጦ ጣለ። 8 ስለዚህ እጮኛዋ ስለ ሞተባት ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ልጃገረድ እናንተም አልቅሱ። 9 በእግዚአብሔር ቤት መባ ሆኖ የሚቀርብ እህልም ሆነ የወይን ጠጅ በመታጣቱ፥ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑት ካህናት ያለቅሳሉ። 10 እርሻዎች ባዶአቸውን ቀርተዋል፤ እህል ጠፍቶአል፤ የወይን ተክሎች ደርቀዋል፤ ዘይትም ጠፍቶአል፤ ስለዚህ ምድር ታለቅሳለች። 11 ስንዴውና ገብሱ፥ ሌላውም መከር ሁሉ ስለ ጠፋ፥ እናንተ ገበሬዎች እዘኑ፤ እናንተም የወይን ተክል ባለቤቶች አልቅሱ። 12 የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች ጠውልገዋል፤ ሮማኑ፥ ተምሩና እንኰዩ፥ ሌሎችም የፍራፍሬ ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ በዚህም ምክንያት በእርግጥ ደስታ ከሰው ልጆች ርቆአል። 13 ለአምላካችሁ የምታቀርቡት የእህልም ሆነ የወይን ጠጅ መባ ስለሌለ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች የሆናችሁ ካህናት! ኑና ማቅ ለብሳችሁ ሌሊቱን ሁሉ አልቅሱ! እናንተም በመሠዊያው ላይ የምታገለግሉ ዋይ! ዋይ! በሉ። 14 የተለየ የጾም ቀን ዐውጁ! መንፈሳዊ ስብስባ ጥሩ! ሽማግሌዎችንና ሌሎችንም የአገሪቱን ኗሪዎች ሁሉ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፤ በዚያም ወደ እግዚአብሔር ጩኹ። 15 ወዮ! የጌታ ቀን ቀርቦአል! ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር ጥፋትን የሚያመጣበት ቀን ደርሶአል። ስለዚያ ቀን ወዮ! 16 እህል ከዐይናችን ደስታና እልልታ ከአምላካችን ቤተ መቅደስ፥ ፈጽሞ ጠፍቶአል። 17 የተዘራው እህል ሁሉ በዐፈር ውስጥ በስብሶ ቀርቶአል፤ እህል በመታጣቱ የእህል ማከማቻዎች ሁሉ ባዶ ሆነዋል፤ ጐተራዎችም ፈራርሰዋል። 18 የግጦሽ ሣር በማጣት ከብቶች ያላዝናሉ፤ የበጎች መንጋ ሳይቀሩ ተርበው በብርቱ ሥቃይ ላይ ይገኛሉ። 19 እግዚአብሔር ሆይ! የሜዳውን ሣር ሁሉ እሳት ስለ በላው፥ የዱሩንም ዛፍ እሳት ስለ አቃጠለው እኔ ወደ አንተ እጮኻለሁ። 20 ወንዞች ስለ ደረቁባቸው፥ የሜዳውም ሣር ሁሉ ስለ ተቃጠለባቸው፥ የዱር አራዊት እንኳ ወደ አንተ ይጮኻሉ። |