ዘዳግም 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየተለዩ የመማጠኛ ከተማዎች ( ዘኍ. 35፥9-28 ፤ ኢያሱ 20፥1-9 ) 1 “እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር የሚኖሩትን ሕዝቦች ደምስሶ ከተሞቻቸውንና ቤቶቻቸውንም ወርሰህ በዚያ መኖር በምትጀምሩበት ጊዜ፥ 2-3 አምላክህ እግዚአብሔር እንድትኖርባት የሚሰጥህን ምድር ለሦስት ትከፍልና በያንዳንዱ ክፍል አንዳንድ ከተማ የተለየ ታደርጋለህ፤ ነፍሰ ገዳይም ይሸሽባቸው ዘንድ ወደ እነዚያ የሚወስዱትን መንገዶች ታዘጋጃለህ፤ ከዚያ በኋላ አንድ ነፍሰ ገዳይ ሕይወቱን ለማትረፍ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ ይሂድ፤ 4 አንድ ሰው ቀድሞ ጠላት ያልነበረውን አንድ ሰው የገደለው ሆን ብሎ በማሰብ ሳይሆን በአጋጣሚ አደጋ ምክንያት ሆኖ ከተገኘ አምልጦ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመግባት ሕይወቱን ያትርፍ። 5 ለምሳሌ፥ ሁለት ሰዎች እንጨት ለመቊረጥ ቢሄዱና አንደኛው እንጨቱን ሲቈርጥ የመጥረቢያው ራስ ከዛቢያው ወልቆ በድንገት ሲወረወር ሌላውን ሰው መትቶ ቢገድል፥ ገዳዩ ከእነዚህ ከሦስት ከተማዎች ወደ አንዲቱ ሄዶ ሕይወቱን ያትርፍ። 6 ያለው የመጠለያ ከተማ፥ ርቀቱ ቶሎ የማይደረስበት ቢሆን ግን፥ ደሙን ለመበቀል መብት ያለው የሟቹ ዘመድ አባሮ ይዞ በደል የሌለበትን ያን ሰው በቊጣ ሊገድለው ይችላል፤ በእርግጥም ያ ሰው ጠላቱ ያልሆነውን ሰው የገደለው በአጋጣሚ ነበር። 7 ሦስት ከተሞችን እንድትለይ የማዝህ በዚህ ምክንያት ነው። 8 “እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ በመሐላ የተስፋ ቃል በገባላቸው መሠረት ግዛትህን ቢያሰፋልህ፥ 9 እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች ሁሉ በመፈጸም እግዚአብሔር አምላክህን ብትወድና በመንገዱ ብትሄድ ይህችን ምድር ስለሚሰጥህ ሌሎች ሦስት የመጠለያ ከተሞች ጨምረህ ሥራ። 10 ይህንንም የምታደርገው እግዚአብሔር አምላክህ እንድትኖርባት ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ንጹሕ ደም እንዳይፈስስና አንተም የደሙ ተጠያቂ እንዳትሆን ነው። 11 “ነገር ግን አንድ ሰው በጠላትነት ተነሣሥቶ በመሸመቅ ሆን ብሎ በጭካኔ ሌላውን ሰው ከገደለ በኋላ ሕይወቱን ለማትረፍ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፤ 12 ገዳዩ የሚኖርበት ከተማ መሪዎች ሰው በመላክ እነርሱም ነፍሰ ገዳዩን አስመጥተው የሟቹን ደም ለመበቀል መብት ላለው የቅርብ ዘመዱ አሳልፈው ይስጡት። 13 ለእርሱ ምንም ምሕረት አታድርግለት፤ በሁሉ ነገር መልካም ይሆንልህ ዘንድ ነፍሰ ገዳይን ከእስራኤል አስወግድ። ቀድሞ የነበረውን ድንበር ማፍረስ እንደማይገባ 14 “እግዚአብሔር አምላክህ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ለአንተ በተሰጠው ድርሻና በጐረቤትህ መካከል በቀድሞ ትውልድ የተተከለውን የድንበር ምልክት አታፍርስ። ስለ ምስክሮች የተሰጠ መመሪያ 15 “የአንድን ሰው ወንጀለኛነት ለማረጋገጥ አንድ ምስክር ብቻ አይበቃም፤ አንድ ሰው ወንጀለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ያስፈልጋሉ። 16 አንድ ክፉ ሰው ሌላውን ሰው በሐሰት ወንጅሎ ቢከሰው፥ 17 ሁለቱም ወገኖች እግዚአብሔር በሚመለክበት ቦታ ወደሚገኙት የወቅቱ ካህናትና ዳኞች ወደሆኑት ፊት ይቅረቡ። 18 ዳኞቹ ጉዳዩን በጥብቅ ይመረምራሉ፤ ያም ሰው እስራኤላዊ በሆነው ወገኑ ላይ የሐሰት ክስ አቅርቦ ከተገኘ፥ 19 ለተከሳሹ ታስቦ የነበረውን ቅጣት እርሱ ይቀበላል፤ ይህን የመሰለ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ዐይነት ታስወግዳለህ። 20 ሰዎች ሁሉ ይህን ስለሚሰሙ ዳግመኛ እንደዚህ ያለ ክፉ ነገር በመካከልህ አያደርጉም፤ 21 በእንደዚህ ያለው ክፉ ነገር ላይ ሁሉ ምንም ዐይነት ምሕረት አይኑርህ፤ የቅጣቱም አፈጻጸም ሕይወት ያጠፋ፥ ሕይወቱ እንዲጠፋ፤ ዐይን ያጠፋ፥ ዐይኑ እንዲጠፋ፤ ጥርስ ያወለቀ፥ ጥርሱ እንዲወልቅ፤ እጅ የቈረጠ፥ እጁ እንዲቈረጥ፤ እግርም የሰበረ፥ እግሩ እንዲሰበር በማድረግ ይሁን። |