ዮሐንስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኒቆዲሞስ በስውር ወደ ኢየሱስ እንደ መጣ 1 ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ ነበረ። 2 ይህ ሰው በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር እነዚህን አንተ የምታደርጋቸውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል ማንም የለም፤ ስለዚህ አንተ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣህ መምህር እንደ ሆንክ እናውቃለን” አለው። 3 ኢየሱስም “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው እንደገና ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። 4 ኒቆዲሞስም “ታዲያ፥ ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግመኛ ወደ እናቱ ማሕፀን ገብቶ መወለድ ይችላልን?” ሲል ጠየቀ። 5 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። 6 ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው። 7 ስለዚህ ‘ዳግመኛ መወለድ ያስፈልጋችኋል’ ስላልኩህ አትደነቅ። 8 ነፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ነገር ግን ከየት እንደሚመጣና ወዴትም እንደሚሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” 9 ኒቆዲሞስም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ጠየቀው። 10 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል መምህር ሆነህ ይህን አታውቅምን? 11 እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ እናንተ ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉትም። 12 ምድራዊውን ነገር ስነግራችሁ የማታምኑ ከሆነ ሰማያዊውን ነገር ስነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13 ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም። 14 “ሙሴ በበረሓ እባብን ከፍ አድርጎ እንደ ሰቀለ እንዲሁም የሰው ልጅ ከፍ ብሎ ሊሰቀል ይገባዋል። 15 ይህም የሚሆነው በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለምን ሕይወት እንዲያገኝ ነው። 16 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ዓለምን እጅግ ስለ ወደደው አንድያ ልጁን ሰጠ። 17 እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው፥ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለም። 18 “በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በእርሱ የማያምን ግን በአንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ ቀድሞውኑ ተፈርዶበታል። 19 “ፍርዱም ይህ ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። 20 ክፉ ነገር የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላል፤ ክፉ ሥራውም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21 እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርግ ግን ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ወደ ብርሃን የሚመጣውም ያደረገው ነገር በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት መሆኑ በግልጥ እንዲታይ ነው።” መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ መመስከሩ 22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ ከእነርሱ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈየ። 23 በዚያኑ ጊዜ ዮሐንስም ብዙ ውሃ ስለ ነበረበት በሳሌም አቅራቢያ ሄኖን በተባለ ስፍራ ያጠምቅ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር። 24 በዚያን ጊዜ ዮሐንስ ገና አልታሰረም ነበር። 25 በዚያን ጊዜ በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ መንጻት ሥርዓት ክርክር ተነሣ። 26 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ዮሐንስ ቀርበው “መምህር ሆይ፥ ያ ከዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው፥ አንተ ስለ እርሱ የመሰከርክለት፥ እነሆ፥ እርሱም ያጠምቃል፤ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዳሉ” አሉት። 27 ዮሐንስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ማንም ሰው እግዚአብሔር ካልሰጠው በቀር ምንም ነገር ሊኖረው አይችልም፤ 28 ‘ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንጂ እኔ መሲሕ አይደለሁም’ ብዬ እንደ ነገርኳችሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮቼ ናችሁ። 29 ሙሽሪት ያለችው ሰው ሙሽራ ነው፤ የሙሽራው ሚዜ ግን ከሙሽራው አጠገብ ቆሞ ይሰማዋል፤ የእርሱንም ድምፅ በመስማት ይደሰታል፤ ስለዚህ የእኔም ደስታ ይህ ነው፤ እርሱም አሁን ፍጹም ሆኖአል። 30 እርሱ ከፍ ከፍ ማለት ይገባዋል፤ እኔ ግን ዝቅ ዝቅ ማለት ይገባኛል።” 31 ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሆነ ምድራዊ ነው፤ የምድርንም ነገር ይናገራል፤ ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። 32 እርሱ ያየውንና የሰማውን ይመሰክራል፤ ነገር ግን የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል የለም። 33 የእርሱን ምስክርነት የሚቀበል ግን እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። 34 እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጠው መጥኖ ስላልሆነ እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። 35 አብ ልጁን ይወዳል፤ ሁሉንም ነገር በእጁ አስረክቦታል። 36 በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በእርሱ ላይ ይኖርበታል እንጂ ሕይወትን አያገኝም። |