Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሐዋርያት ሥራ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሽባው መፈወስ

1 አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤

2 እዚያ “ውብ” እየተባለ የሚጠራ በር ነበር፤ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የሆነውን አንድ ሰው ሰዎች በየቀኑ እያመጡ እዚያ ያስቀምጡት ነበር፤ እርሱ እዚያ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት ይለምን ነበር።

3 ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው።

4 እነርሱም ሰውየውን ትኲር ብለው አዩትና ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት!” አለው።

5 እርሱም ምጽዋት የሚሰጡት መስሎት ትኲር ብሎ አያቸው።

6 ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተራመድ!” አለው።

7 ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውኑ እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ።

8 ብድግ ብሎም ቆመ፤ እየተራመደም ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ እየተራመደና እየዘለለም እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር።

9 ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አዩት።

10 “ውብ በር” እየተባለ በሚጠራው በቤተ መቅደሱ በር አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይም በተደረገው ነገር ይገረሙና ይደነቁ ጀመር።


ጴጥሮስ በቤተ መቅደስ ያደረገው ንግግር

11 የዳነው ሰው ከጴጥሮስና ከዮሐንስ አልለይም በማለት ይዞአቸው ሳለ ሰዎቹ ተደንቀው “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደሚባለው ስፍራ ወደ እነርሱ ሮጠው ሄዱ፤

12 ጴጥሮስም ሰዎቹን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ነገር ስለምን ትደነቃላችሁ? ስለምንስ ትኲር ብላችሁ ታዩናላችሁ? እኛ በራሳችን ኀይል ወይም በራሳችን መልካም ሥራ ይህን ሰው እንዲራመድ ያደረግነው ይመስላችኋልን?

13 የአባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና፥ የያዕቆብ አምላክ ልጁን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እርሱን በጲላጦስ ፊት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስም ሊለቀው ቢፈልግ እንኳ ‘አንፈልግም’ አላችሁ።

14 እናንተ ቅዱሱንና ጻድቁን ‘አንፈልገውም’ ብላችሁ አንድ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ።

15 ሕይወት ሰጪ የሆነውንም ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን።

16 ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው ድኖ የበረታው በኢየሱስ ስም በተገኘው እምነት ነው፤ በኢየሱስ ስም በማመኑም በሁላችሁ ፊት ሙሉ ጤንነት አግኝቶአል።

17 “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ላይ ያደረጋችኹትን ነገር እናንተም እንዳለቆቻችሁ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት ዐውቃለሁ።

18 እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ ‘መሲሑ መከራ መቀበል አለበት’ ያለው ቃል በዚህ ዐይነት እንዲፈጸም አደረገ።

19 እንግዲህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስላችሁ ንስሓ ገብታችሁ ወደ ጌታ ተመለሱ፤

20 ከእግዚአብሔርም ዘንድ የምትታደሱበት ዘመን ይመጣላችኋል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን መሲሕ ኢየሱስን ይልክላችኋል።

21 እርሱም በሰማይ የሚቈየው እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረው ዓለም ሁሉ እስኪታደስ ድረስ ነው።

22 ሙሴም እንዲህ ብሎአል፦ ‘ጌታ አምላክህ እኔን እንዳስነሣኝ እንዲሁ ከወንድሞቻችሁ መካከል ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙ፤

23 ያን ነቢይ የማይሰማ ሁሉ ከሕዝብ ተለይቶ ፈጽሞ ይጠፋል።’

24 ቀጥሎም ከሳሙኤል ጀምሮ የነበሩ ነቢያት ሁሉ፥ ስለዚህ ዘመን እንዲሁ ተናግረዋል።

25 እናንተ የነቢያት ወራሾች ናችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለአብርሃም ‘በምድር ላይ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ’ ብሎ ከአባቶቻችን ጋር የገባው የቃል ኪዳን ወራሾች ናችሁ።

26 ስለዚህ እግዚአብሔር ልጁን የላከው በመጀመሪያ ለእናንተ ነበር፤ ይህንንም ያደረገው እያንዳንዳችሁን ከክፉ መንገዳችሁ በመመለስ እንዲባርካችሁ ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos