ዳንኤል 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመጨረሻው ዘመን 1 ያ ራእዩን ያብራራልኝ የነበረው መልአክ እንደገና እንዲህ አለኝ፦ “ሕዝብህን የሚጠብቀው ታላቁ አለቃ ሚካኤል በዚያን ጊዜ ይገለጣል፤ የሰው ዘር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ ነገር ግን ስማቸው በእግዚአብሔር መጽሐፍ የተጻፈ የአገርህ ሕዝቦች ብቻ በዚያን ጊዜ ይድናሉ፤ 2 ሞተው ዐፈር የበላቸው ሁሉ ይነሣሉ፤ ከእነርሱም ከፊሎቹ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ሲገቡ ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ዘለዓለማዊ ኀፍረትና ውርደት ይላካሉ። 3 በዚያን ጊዜ ጠቢባን እንደ ሰማይ ብርሃን ያንጸባርቃሉ፤ ብዙ ሰዎችን በማስተማር ከክፉ መንገድ ወደ ደግ ሥራ የመለሱ ሁሉ ለዘለዓለም እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበራሉ።” 4 እንደገናም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! የዓለም መጨረሻ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ መጽሐፉን ዘግተህ አሽገው፤ የትንቢቱንም ቃል በምሥጢር ያዝ፤ በዚያን ጊዜ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይራወጣሉ፤ ምርምርና ዕውቀትም ይበዛል።” 5 ከዚያን በኋላ በወንዝ ዳር ሁለት ሰዎች ማዶ ለማዶ ቆመው አየሁ፤ 6 ከእነርሱ አንዱ ቀጭን ሐር ለብሶ ከወንዙ በላይ በኩል የቆመውን መልአክ “ይህ ሁሉ አስደናቂ ነገር ፍጻሜ እስከሚያገኝ ምን ያኽል ጊዜ ይወስዳል?” ብሎ ጠየቀው። 7 ቀጭን ሐር ለብሶ ከወንዝ በላይ በኩል የቆመው መልአክ ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ በዘለዓለማዊው አምላክ ስም በመማል “ሦስት ዓመት ተኩል ይወስዳል፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሚደርሰው መከራ ሲያከትም እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተፈጻሚነት ያገኛሉ።” 8 መልአኩ የተናገረውን ሁሉ ሰማሁ፤ ነገር ግን ሊገባኝ አልቻለም፤ ስለዚህ “ጌታዬ ሆይ! የዚህ ሁሉ የመጨረሻው ውጤት ምን ይሆን?” ብዬ ጠየቅሁት። 9 እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! የዓለም መጨረሻ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ ቃሉ የትንቢቱም ቃል ምሥጢር ሆኖ ስለሚጠበቅ እንግዲህ አንተ ሂድ። 10 ብዙዎች ነጥረውና ጠርተው በመውጣት ነውር የሌለባቸው ይሆናሉ፤ ክፉዎች ግን ምንም ስለማያስተውሉ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ የማስተዋል ችሎታ የሚኖራቸው ጠቢባን ብቻ ናቸው። 11 “የዘወትሩ መሥዋዕት ተቋርጦ አጸያፊ የሆነው የጥፋት ርኲሰት እንዲቆም ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀኖች ያልፋሉ። 12 አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀኖች እስከሚያልፉ ድረስ እምነቱን ጠብቆ የሚኖር የተባረከ ነው። 13 “አንተም ዳንኤል ሆይ! እስከ መጨረሻው በታማኝነትህ ጸንተህ ኑር፤ ከዚያ በኋላ ታርፋለህ፤ በዚህ ዐይነት ከሞትህ ተነሥተህ በመጨረሻው ቀን የክብር ዋጋህን ታገኛለህ።” |