Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሐዋርያት ሥራ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ቴዎፍሎስ ሆይ! በመጀመሪያ መጽሐፌ ኢየሱስ የሠራውንና ያስተማረውን ሁሉ ጽፌአለሁ። የጻፍኩትም ኢየሱስ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ

2 ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ የሠራውን ነው፤ ወደ ሰማይ ያረገውም ለመረጣቸው ሐዋርያት ትእዛዙን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከሰጣቸው በኋላ ነው፤

3 ብዙ መከራ ተቀብሎ ከሞተ በኋላ በብዙ ግልጥ ማስረጃዎች ሕያው ሆኖ ታያቸው፤ አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው።

4 አብሮአቸውም በነበረ ጊዜ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “እኔ የነገርኳችሁን ከአብ የተሰጠ ተስፋ ጠብቁ እንጂ ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤

5 ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።”


ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ
( ማር. 16፥19-20 ፤ ሉቃ. 24፥50-53 )

6 እነርሱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ! መንግሥትን ለእስራኤል መልሰህ የምትሰጥበት ጊዜ አሁን ነውን?” ሲሉ ጠየቁት።

7 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜና ዘመን እናንተ ልታውቁት አትችሉም።

8 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።”

9 ይህንንም ካለ በኋላ እነርሱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ደመናም ተቀብሎ ከዐይናቸው ሰወረው።

10 እርሱ እያረገ ሳለ፥ እነርሱ ትኲር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች አጠገባቸው ቆመው፥

11 “እናንተ የገሊላ ሰዎች፥ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው።


በይሁዳ ምትክ ማትያስ መመረጡ
( መዝ. 109፥8 )

12 ከዚህ በኋላ ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም የሚርቀው የሰንበት መንገድ (አንድ ኪሎ ሜትር) ያኽል ነው።

13 ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ወደሚኖሩበት ሰገነት ላይ ወጡ፤ እነርሱም “ጴጥሮስ፥ ዮሐንስ፥ ያዕቆብ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ ቶማስ፥ በርተሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ቀናተኛው ስምዖንና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ” ናቸው።

14 እነዚህ ሁሉ ዘወትር ለጸሎት በአንድነት ይሰበሰቡ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር አንዳንድ ሴቶችና የኢየሱስ እናት ማርያም፥ እንዲሁም የኢየሱስ ወንድሞች ነበሩ።

15 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መቶ ኻያ በሚያኽሉ አማኞች መካከል ቆመና እንዲህ አለ፦

16 “ወንድሞች ሆይ፥ ኢየሱስን ለያዙት ሰዎች መሪ ስለ ሆናቸው ስለ ይሁዳ፥ መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም ነበረበት።

17 ይሁዳ ከእኛ አንዱ ሆኖ የዚህ አገልግሎታችን ተካፋይ ነበር።

18 ነገር ግን ይህ ሰው በክፉ ሥራው ዋጋ መሬት ገዛ፤ በግንባሩም ተደፍቶ ከመካከሉ ተሰነጠቀ፤ አንጀቱም ተዘረገፈ፤

19 ይህም ነገር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ታወቀ፤ ስለዚህ ያ መሬት በቋንቋቸው ‘አኬልዳማ’ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጓሜውም ‘የደም መሬት’ ማለት ነው።

20 “ይህም የሆነበት ምክንያት በመዝሙር መጽሐፍ፥ ‘መኖሪያው ባዶ ይሁን፤ ማንም አይኑርበት፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ሰው ይውሰድበት’ የሚል ተጽፎ ስለ ነበር ነው።

21 “ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በእኛ መካከል በተመላለሰበት ጊዜ ሁሉ ከእኛ ጋር አብረውን ከነበሩት፥

22 እንዲሁም ከዮሐንስ ጥምቀት ጀምሮ ጌታ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እስከ ዐረገበት ቀን ድረስ አብረውን ከነበሩት ከነዚህ ሰዎች አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን ያስፈልጋል።”

23 ከዚህ በኋላ ሁለት ሰዎች አቀረቡ፤ እነርሱም በርሳባስ ወይም ኢዮስጦስ የሚባለው ዮሴፍና ማትያስ ነበሩ።

24 እንዲህ ሲሉም ጸለዩ፦ “የሰውን ሁሉ ልብ የምታውቅ ጌታ ሆይ፥ ከነዚህ ከሁለቱ ማንን እንደ መረጥክ አሳየን፤

25 የምንጸልየውም ይሁዳ ወደ ራሱ ስፍራ ሲሄድ የተወውን አገልግሎትና ሐዋርያነት በመቀበል የሚተካውን እንድትገልጥልን ነው።”

26 ዕጣም በጣሉ ጊዜ ዕጣው ለማትያስ ወጣ፤ ስለዚህ እርሱ ከዐሥራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቈጠረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos