ዘኍል 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምታብዔራ 1 እስራኤላውያን ስለ ደረሰባቸው ችግር ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ እግዚአብሔርም የማጒረምረም ጩኸታቸውን ሰምቶ እጅግ በመቈጣት የሚባላ እሳት ላከባቸው፤ ያም እሳት ከሰፈሩ አንዱን ክፍል አወደመ። 2 ሕዝቡም ያማልዳቸው ዘንድ ወደ ሙሴ ጮኹ፤ ሙሴም እግዚአብሔርን ለመነ፤ እሳቱም ተገታ። 3 የእግዚአብሔር እሳት በዚያ ስፍራ በመካከላቸው ስለ ነደደ ያ ስፍራ “ታብዔራ” ተብሎ ተጠራ። ሙሴ ሰባ የሕዝብ አለቆችን ለመሪነት መምረጡ 4 ከእስራኤላውያን ጋር የሚጓዙ የውጪ አገር ሰዎች ሥጋ ለመብላት የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፤ እስራኤላውያንም እንዲህ እያሉ ማልቀስ ጀመሩ፦ “የምንበላውን ሥጋ ከየት እናገኛለን! 5 በግብጽ ሳለን ምንም ዋጋ ሳንከፍል የፈለግነውን ያኽል ዓሣ እንበላ እንደ ነበረ እናስታውሳለን፤ በዚያ ሳለን እንበላ የነበረውን ዱባ፥ (ኪያር) ሀብሀብ (በጢኽ)፥ ኲራት (ድንች መሳይ ምግብ) ቀዩንና ነጩን ሽንኩርት፥ 6 አሁን ግን ሰውነታችን ደርቆ ኀይላችን ደከመ፤ የምንመገበው ምንም ነገር የለም፤ በየቀኑ ከዚህ መና በቀር ሌላ የምናየው የለም።” 7 መና እንደ ድንብላል ዘር ትንንሽ ሆኖ እንደ ሙጫ ነጣ ያለ ቢጫ መልክ ነበረው፤ 8 ሰዎቹም እየዞሩ ይለቅሙ ነበር፤ በወፍጮም ይፈጩት ወይም በሙቀጫ ይወቅጡት፥ በምንቸትም ያፈሉትና ይጋግሩት ነበር፤ ጣዕሙም በዘይት እንደ ተለወሰ ቂጣ ነበር፤ 9 ሌሊት ጠል በሰፈሩ ላይ በሚወርድበት ጊዜ መናውም አብሮት ይወርድ ነበር። 10 ሕዝቡ ሁሉ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ በየቤተሰባቸው ቆመው ሲያለቅሱ ሙሴ ሰማቸው፤ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጥቶ ስለ ነበረ ሙሴ በጣም ተጨነቀ። 11 እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ “ይህን ከባድ ነገር በእኔ በአገልጋይህ ላይ ስለምን አመጣህብኝ? ለምንስ በፊትህ ሞገስን አላገኘሁም? የዚህን ሁሉ ሕዝብስ ከባድ ኀላፊነት ለምን በእኔ ላይ ጫንከው? 12 ጡት የሚጠባውን ሕፃን አንዲት ሞግዚት እንደምትታቀፈው እኔም እነርሱን ታቅፌ አንተ ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳደርሳቸው የምታደርገኝ እነዚህን ሰዎች እኔ ፀነስኳቸውን? ወይስ እኔ ወለድኳቸውን? 13 የምንበላውን ሥጋ ስጠን እያሉ ወደ እኔ መጥተው ስለሚያለቅሱ ለእነዚህ ሰዎች ሁሉ የሚሆን ሥጋ ከወዴት አመጣለሁ? 14 እኔ ይህን ሁሉ ሕዝብ ብቻዬን መምራት አልችልም፤ ይህ ኀላፊነት ለእኔ እጅግ ከባድ ነው፤ 15 በዚህ ሁኔታ እንድሠቃይ ከምታደርገኝ ይልቅ መከራ እንዳላይ ብትራራልኝና አሁኑኑ ብትገድለኝ ይሻላል።” የሰባ ሽማግሌዎች መመረጥ 16 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሕዝብ አመራር በመስጠት የታወቁ ሰባ ሽማግሌዎችን ምረጥ፤ እነርሱንም ሰብስበህ ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸውና በአጠገብህ ይቁሙ፤ 17 እኔም ወደዚያ ወርጄ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤ ለአንተም ከሰጠሁህ መንፈስ ከፍዬ ለእነርሱ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእነዚህ ሕዝብ ላይ ያለህን ኀላፊነት በመሸከም ይረዱሃል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ይህን ሁሉ ኀላፊነት ብቻህን አትሸከምም። 18 አሁንም ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ለነገ ራሳችሁን አንጹ፤ የምትበሉትም ሥጋ ይኖራችኋል፤ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል ብላችሁ ማልቀሳችሁንና የግብጽ ምድር ይሻለን ነበር ማለታችሁን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እርሱንም ትበላላችሁ። 19 የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ለአምስት፥ ለዐሥር ወይም ለኻያ ቀን ብቻ አይደለም፤ 20 እስኪያንገፈግፋችሁና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ አንድ ወር ሙሉ ትመገቡታላችሁ፤ ይህም የሚሆነው እዚህ በመካከላችሁ ያለውን ጌታ ስለ ናቃችሁና፦ ከግብጽ ባልወጣን ኖሮ መልካም ነበር በማለት ስላለቀሳችሁ ነው።’ ” 21 ሙሴም ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ ስድስት መቶ ሺህ ሕዝብ በመምራት ላይ እገኛለሁ፤ ለአንድ ወር የሚበቃ ሥጋ ልትሰጣቸው ቃል ገብተሃል፤ 22 ታዲያ ምን ያኽል የከብትና የበግ መንጋ ቢታረድ እነርሱን ሊያጠግብ ይችላል? በባሕር ውስጥ ያለው ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ለእነርሱ በቂ ሊሆን ይችላልን?” 23 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእኔ የእግዚአብሔር ኀይል ውሱን ነውን? ቃሌ በእናንተ ዘንድ የሚፈጸም ወይም የማይፈጸም መሆኑን አሁን ታያለህ!” 24 ስለዚህ ሙሴ ወጥቶ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ መሪዎች ሰባውን በአንድነት ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። 25 እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ተናገረው፤ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ከፊሉን ወስዶ በሰባዎቹ መሪዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈስ በወረደባቸውም ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ፤ ይህን ያደረጉት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር። 26 ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ። 27 አንድ ወጣት ወደ ሙሴ ሲሮጥ ሄዶ “ኤልዳድና ሜዳድ በሰፈር ውስጥ ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ሲል ነገረው። 28 ከጐልማሳነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው!” አለው። 29 ሙሴም “አንተ ስለ እኔ ትቈረቈራለህን? እኔስ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ መንፈሱን ቢያወርድና ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታዬ ነው!” አለው። 30 ሙሴና ሰባዎቹ የእስራኤል መሪዎችም ወደ ሰፈር ተመለሱ። እግዚአብሔር ድርጭቶችን እንደ ሰጠ 31 በድንገትም እግዚአብሔር ድርጭቶችን ከባሕር እየነዳ የሚያመጣ ነፋስ ላከ፤ ድርጭቶችም ከምድር አንድ ሜትር ያኽል ከፍ ብለው እየበረሩ መጡ፤ በሰፈሩና በሰፈሩ ዙሪያ የተከማቹበት ስፍራ የአንድ ቀን መንገድ ያኽል ነው፤ 32 ስለዚህ በዚያን ቀንና ሌሊት፥ እንዲሁም በማግስቱ ሕዝቡ ድርጭት እያሳደዱ በመያዝ ደከሙ፤ ከዐሥር ኪሎ ግራም ያነሰ የሰበሰበ አልነበረም፤ እንዲደርቁም በሰፈር ዙሪያ አሰጡአቸው። 33 የሚበሉት ሥጋ ገና በብዛት ሳለ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ እጅግ ተቈጣ፤ ብርቱ መቅሠፍትም በሕዝቡ መካከል አመጣ፤ 34 በሥጋ አምሮት የሞቱትን ሕዝብ እዚያ ቀብረዋቸው ስለ ነበር የዚያ ስፍራ ስም “የምኞት መቃብር” ተባለ፤ 35 ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሐጼሮት ተጒዘው በዚያ ሰፈሩ። |