ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከዚህም በኋላ ፈጣሪ ለዚያ ንስር ይህን ቃል በነገረው ጊዜ፥ 2 የቀረው ያ ራስ ጠፋ፤ወደ እርሱ የመጡ እነዚያም ክንፎች ተነሡ፤ እነርሱም ይገዙ ዘንድ ተነሡ፤ በጥፍራቸውም ይታወኩ ነበር። 3 ከዚህ በኋላ እነርሱም ጠፉ፤ ሥጋቸውም ሁሉ ተቃጠለ፤ ምድርም ፈጽማ ደነገጠች። እኔም ከብዙ ምርምር የተነሣ ደነገጥሁ፤ በጽኑ ፍርሀትም ነቃሁ። 4 ልቡናዬንም እንዲህ አልኋት፥ “የልዑልን ሥራ ስትመረምሪ አንቺ ይህን ሁሉ አደረግሽኝ። 5 ሰውነቴም ደከመች፤ ልቡናዬም እጅግ ተጨነቀች፤ በብዙ ፍርሀት ተይዤ ምንም ኀይል የለኝም፤ በዚችም ሌሊት ደነገጥሁ። 6 አሁንም ለዘለዓለሙ ያጸናኝ ዘንድ ወደ ልዑል እጸልያለሁ።” 7 እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ በዐይኖችህ ፊት ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ በአንተም ዘንድ ራሴን ብፁዕ ካሰኘሁ፥ ጸሎቴም በፊትህ ከደረሰች፥ 8 አድነኝ፤ አጽናኝም፤ ነፍሴም ፈጽማ ደስ ይላት ዘንድ የሚያስፈራ የዚህን ሕልም ትርጓሜ ለባሪያህ ንገረው። 9 በኋላ ዘመን የሚደረገውንና የዓለሙን ኅልፈት ያሳየኸኝ አንተ ብፁዕ አድርገኸኛልና።” የራእዩ ትርጓሜ 10 መልአኩም እንዲህ አለኝ፥ “ያየኸው የዚህ ሕልምህ ትርጓሜ እንዲህ ነው። 11 ከባሕር ሲወጣ ያየኸው ይህ ንስር ለወንድምህ ለዳንኤል በሕልም የታየችው አራተኛዋ መንግሥት ናት። 12 ነገር ግን ዛሬ ለአንተ እኔ እንደተረጐምሁልህ ለእርሱ አልተረጐምሁለትም። 13 እነሆ፥ ዘመን ይመጣል፤ በምድርም ከእርስዋ አስቀድሞ ከነበሩት መንግሥታት ይልቅ የምታስፈራ መንግሥት ትነሣለች። 14 በእርሷም ዐሥራ ሁለት ነገሥታት በተከታታይ ይነግሣሉ። 15 ቀጥሎ የሚነግሠውም በዘመኑ ከዐሥራ ሁለቱ ነገሥታት ፈጽሞ የሚጸና ነው። 16 ያየሃቸው የእኒህ የዐሥራ ሁለቱ ክንፎች ትርጓሜ ይህ ነው። 17 ቃልን ሲናገር ያየኸው ይህም ከሥጋው መካከል ነው እንጂ ከራሱ የሚወጣ ሁለተኛው አይደለም። 18 ትርጓሜውም እንዲህ ነው፤ ከዚያ መንግሥት ወገን መካከል ብዙ ሁከት ይፈጠራል፤ መንግሥትም ለመውደቅ ትንገዳገዳለች፤ ነገር ግን ጸንታ ትኖራለች እንጂ ያንጊዜ አትወድቅም። 19 ከክንፎቹም ራሶች ሲወጡ ያየኸው ይህ፥ 20 ትርጓሜው እንደዚህ ነው፤ ስምንቱ ነገሥታት በእርስዋ ይነግሣሉ፤ ዘመናቸውም የከፋ፥ ወራታቸውም ያጠረ ይሆናል፤ ከእነርሱ ሁለቱ ግን በዘመናቸው መካከል ፈጥነው ይጠፋሉ። 21 ነገር ግን አራቱ መንግሥታት የሚጠፉበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይጠበቃሉ፤ ሁለቱም ለብዙ ዘመን ይጠበቃሉ። 22 “ዝም ብለው ያየሃቸው እነዚህ ሦስቱ ራሶችም፦ 23 ትርጓሜው እንዲህ ነው፤ ልዑል በኋላ ዘመን ሦስት ነገሥታትን ያስነሣል፤ በውስጧም ብዙውን ያድሳሉ፤ ምድርንም ያሠቃዩአታል። 24 በውስጧ የሚኖሩትንም ከእነርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ያሠቃዩአቸዋል። ስለዚህም የንስሩ ራሶች ተባሉ። 25 እነርሱ የመንግሥት መጀመሪያዎች፥ የመንግሥትም መጨረሻዎች ናቸውና። 26 ይህም ሲጠፋ ያየኸው አንዱ ታላቅ ራስ በታላቅ ጻእር ተጨንቆ በመኝታው የሚሞት ከእነርሱ አንዱ ነው። 27 የቀሩት እነዚያ ሁለቱ ግን በጦር ይሞታሉ። 28 አንዱ ኋለኛውም በጦር ይሞታል። 29 “በቀኝ በኩል ወደ አለው ራሱ የሄዱት እነዚያ ያየሃቸው ሁለት ራሶችም፥ 30 ትርጓሜው ይህ ነው፤ ልዑል በኋላ ዘመን የጠበቃቸው፥ መጀመሪያው ጥፋት የሚደረግባቸው ናቸው፤ አንተ እንዳየኸውም ብዙ ጸብ ይደረጋል። 31 ከዱር እያገሣ ሲወጣ ያንም ንስር በሰማኸው ሁሉ ነገር ሲናገረውና በኀጢአቱ ሁሉ ሲዘልፈው ያየኸው ይህ አንበሳም፥ 32 ልዑል ለኋላ ዘመን የጠበቀው፥ ከዳዊትም ወገን የሚወለደው ነው፤ መጥቶም ኀጢአታቸውን ይነግራቸዋል፤ ስለበደላቸውም ይዘልፋቸዋል፤ በፊታቸውም ፍዳቸውን ይገልጥባቸዋል። 33 በሕይወት ሳሉም አስቀድሞ በፍርድ ያቆማቸዋል፤ ከዘለፋቸውም በኋላ ያንጊዜ ያጠፋቸዋል። 34 ትሩፋኑን ግን በቸርነቱ በከበረ አውራጃ ይቤዣቸዋል፤ አስቀድሜም የነገርሁህ የፍርድ ቀን እስኪደርስ ድረስ ደስ ያሰኛቸዋል። 35 ያየኸው ሕልምህ ይህ ነው፤ ትርጓሜውም እንደዚህ ነው። 36 ልዑል ይህን ምሥጢር አንተ ብቻ እንድታውቀው አደረገልህ። 37 ነገር ግን ይህን ያየኸውን ሁሉ ጻፈው፤ በተሰወረ ቦታም አኑረው። 38 ይህንም ምሥጢር በልቡናቸው ለመጠበቅ እንዲቻላቸው አንተ ለምታውቃቸው ለጠቢባን አስተምራቸው። 39 አንተ ግን ልዑል ሊያሳይህ የሚወድደውን ታይ ዘንድ ዳግመኛ ሰባት ቀን በዚህ ተቀመጥ።” ሕዝቡ ወደ ዕዝራ እንደ ተሰበሰቡ 40 ከዚህም በኋላ ከእኔ ተለይቶ ሄደ፤ እኒያ ሰባት ቀኖች እንዳለፉ፥ እኔም ወደ ከተማ እንዳልገባሁ ሰዎች ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ ሕዝቡ ሁሉ ትንሹም ትልቁም ተሰብስበው ወደ እኔ መጡ፤ እንዲህም አሉኝ፦ 41 “እኛን ትተኸን በዚህ ምድረ በዳ ትኖር ዘንድ ምን በደልንህ? ምንስ ግፍ ሠራንብህ? 42 ከሚለቅሙት ፍሬ ሁሉ እንደ አንድ ፍሬ፥ በጨለማ ቦታ ውስጥም እንደ አለ መብራት፥ ከጥልቅም እንደሚያድን የመርከብ ወደብ ከነቢያት ሁሉ አንድ አንተ ብቻ ቀርተህልናልና። 43 ወይስ ያገኘችን መከራ አልበቃችንምን? 44 አንተስ የምትለየን ከሆነ ጽዮን በተቃጠለች ጊዜ ብንኖር በተሻለን ነበር፤ 45 በዚያ ከሞቱት ሰዎች እኛ የምንሻል አይደለንምና።” በታላቅ ድምፅም አለቀሱ። 46 እኔም መለስሁላቸው፤ እንዲህም አልሁአቸው፥ “የያዕቆብ ልጆች እመኑ፤ የእስራኤልም ወገኖች አትዘኑ። 47 መታሰቢያችን በልዑል ፊት አለና፥ የማይዘነጋን እርሱም ጽኑዕ ነውና። 48 እኔስ አልተዋችሁም፤ ከእናንተም አልርቅም፤ ነገር ግን ወደዚህ ቦታ የመጣሁት ስለ ጽዮን ጥፋት እለምን ዘንድ ነው፤ በደስታችን ላይ ስለ መጣብንም መከራ ይቅርታን እለምን ዘንድ ነው። 49 አሁንም ሁላችሁ ወደየቤታችሁ ግቡ፤ እኔም ወደ እናንተ እመጣለሁ።” 50 ከእነዚያም ወራቶች በኋላ ሕዝቡ እንዳዘዝኋቸው ወደ ከተማ ወደየቤታቸው ገቡ። 51 እኔ ግን መልአኩ እንዳዘዘኝ በዚያ ቦታ በምድረ በዳው ውስጥ ሰባት ቀን ተቀመጥሁ፤ ከምድረ በዳ ፍሬ ብቻም ተመገብሁ፤ በእነዚያም በሰባቱ ቀኖች ከምድረ በዳው ቅጠል በላሁ። |