ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን፣ ከፍቅር የመነጨውን ድካማችሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ።
ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋራ የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።
በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።
በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤
በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣
በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣
በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።
አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል።
አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይሥሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤
ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው።
ስለዚህ ተስፋው በእምነት መጥቷል፤ ይኸውም ተስፋው በጸጋ እንዲሆንና ለአብርሃም ዘር ሁሉ ዋስትና ይሆን ዘንድ ነው፤ ይህም በሕግ የርሱ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን፣ በእምነት የአብርሃም ለሆኑትም ነው፤ እርሱም የሁላችን አባት ነው።
ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን።
እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል። አምናችሁም በርሱ በመሆን፣ ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል።
ሔኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ “እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም”፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሠኘ ተመስክሮለታልና።
ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤
የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል።
ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤
በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?”
እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤
የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።
ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።
እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እምነታችሁ በማነሱ ምክንያት ነው፤ እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል እምነት ቢኖራችሁ፣ ይህን ተራራ፣ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም፤ [
ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።
ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብርን ሰጠ እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ አልተጠራጠረም፤
እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም በሙሉ ልብ ርግጠኛ ነበር።
አብርሃም ምንም እንኳ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሣራም ራሷ መካን ብትሆንም፣ ተስፋን የሰጠውን ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረ በእምነት የልጅ አባት ለመሆን በቃ።
ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤
ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።
እኛ ግን የቀን ሰዎች ስለ ሆንን፣ እምነትንና ፍቅርን እንደ ጥሩር ለብሰን፣ የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቍር ደፍተን፣ ራሳችንን በመግዛት እንኑር፤
ሕግ በመጠበቅ የሚገኝ የራሴ ጽድቅ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ ከእምነትም በሆነ ጽድቅ በርሱ ዘንድ እንድገኝ ነው።
ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።