Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ጥበብ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እስራኤል ድኅነትና ስለ ግብፃውያን ጥፋት 1 ስለዚህም አምልኮታቸውን በሚመስል በሚገባ ተቀጡ፥ በብዙ ተናካሽ ትንኞችም ተሠቃዩ። 2 ለሕዝብህም በጠላቶቻቸው ፊት በጎ አደረግህላቸው፥ ለፍላጎታቸውም ድርጭትን ሰጠሃቸው። ጣዕሙ ልዩ የሆነ መናንም ይበሉ ዘንድ ሰጠሃቸው። 3 እነዚያ ግን መብልን በተመኙ ጊዜ በእነርሱ ስለ ተላከባቸው ፍጥረት ከፍላጎታቸው ተመለሱ፥ የዘወትሩንም ልማድ ናቁ። እነዚህ ግን ምግብን በማጣት ጥቂት ወራት ከተቸገሩ በኋላ ጣዕሙ ልዩ ለሆነ ምግብ ተዘጋጁ። 4 በእነዚህ ላይ ፍርድ ያለ ርኅራኄ ይደርስ ዘንድ ግድ ነው። ክፉዎችና በኀይል የሚገዙ ናቸውና። ነገር ግን ለእነዚህ የሚገባው ጠላቶቻቸው እንዴት እንደሚሠቃዩ ያዩ ዘንድ ብቻ ነው። 5 የክፉዎች አራዊት ቍጣ ቢመጣባቸው፥ በክፉዎች እባቦች መንደፍም ቢያልቁ፥ ለጥቂት ወራት ይቀጡ ዘንድ ታወኩ እንጂ ቍጣህ ለብዙ ጊዜ የጸናባቸው አይደለም፤ 6 ይህም ምልክት የሕግህን ትእዛዝ ያሳስባቸው ዘንድ ለድኅነት ማስጠንቀቂያ ሆናቸው። 7 ሁሉን የምታድን ሆይ፥ ከእነርሱ የተመለሰው በአንተ ዳነ እንጂ በማየት ብቻ የዳነ አይደለም። 8 በዚህም ፈተንኻቸው፥ ከክፉ ሁሉ የምታድን አንተ እንደ ሆንህም ጠላቶቻችንን አሳመንኻቸው። 9 የተቈናጣጭ ዝንብና የአንበጣ ንክሻ እነዚህን አጥፍትዋቸዋልና፤ ለነፍሳቸውም ድኅነትን አላገኙም፤ በእንደዚህ ያለ ምሳሌ ልትፈርድባቸው ይገባቸዋልና። 10 በልጆችህ ግን መርዝ ያለው የእባቦች ጥርስ በታዘዘ ጊዜ አልጐዳቸውም፥ ቸርነትህ መጥቶ አድኖአቸዋልና። 11 ሕግህን ለማሰብ ይህን ቀምሰዋልና፥ በጽኑ ዝንጋዔም እንዳይወድቁ፥ ተአምራትህንም ከማሰብ ወጥተው በሌላ ሥራና መከራ እንዳይወድቁ ፈጥነው ዳኑ። 12 አቤቱ፥ ሁሉን የሚያድን ቃልህ ነው እንጂ የሚጠጡት እንጨት ፥ የሚቀቡትም መድኀኒት ያዳናቸው አይደለም። 13 በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን አለህና፥ ወደ ሲኦል በሮች ታወርዳለህ፥ ከሲኦልም ታወጣለህ። 14 ሰው ግን በክፉ ይገድላል፥ ነፍስ ከሥጋ ከተለየ በኋላ አይመለስም፥ የተለየች ነፍስም አትመለስም። 15 ከእጅህ ግን መሸሽ አይቻልም። ማዕበል ግብፃውያንን እንደ መታ 16 ዝንጉዎች እንዲክዱህ ባወቅህ ጊዜ በክንድህ ኀይል ተቀሠፉ፤ በልዩ ዝናምና በረድ፥ ያለ ምሕረትና ያለ መገታት በወረደ በሰማይ ሿሿቴ ጠፉ፥ በእሳትም አለቁ። 17 ድንቅ ሥራስ ሁሉን በሚያጠፋ በውኃ ውስጥ የእሳት ኀያል መሆንና መሠልጠን ነው። ዓለም ለጻድቃን ረዳት ነውና። 18 የእሳት ነበልባል በዝንጉዎች ላይ የተላኩ እንስሳትን እንዳያቃጥል ለማዳ ሆነ፥ ነገር ግን ይህን ባዩ ጊዜ በእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚጠፉ ያውቃሉ። 19 የዐመፀኛዋን ምድር ፍሬ ያጠፋ ዘንድ የእሳቱ ኀይል በውኃው መካከል የሚነድድበት ጊዜ ነበር። ለእስራኤል መና ስለ መውረዱ 20 ስለ ፍሬውም ፋንታ የመላእክትን ምግብ ለሕዝብህ መገብኻቸው፥ ያለ ድካም የተዘጋጀ፥ ጣዕሙም ከሚጣፍጠው ሁሉ የሚበልጥ፥ ጣዕምንም ሁሉ የሚያስንቅ ኅብስትን ከሰማይ ላክህላቸው። 21 የሰማያዊው መልክህ አርአያ የሚሆን መና ለልጆችህ የፍቅርህን ጣዕም ገለጠ፥ ከእርሱም ለሚበላ ጣዕሙ ይዘዋወር ነበር፥ ከምግቦችም ይልቅ ያሰበውንና የወደደውን ፍላጎቱን ለመፈጸም ያገለግለው ነበር። 22 በረድና ውርጭ ከእሳት ጋር ጸንተው ቆሙ፤ እሳቲቱ በበረዱ መካከል እየነደደች፥ በዝናሞችም መካከል ቦግ ቦግ እያለች፥ የጠላቶችን አዝመራ ፍሬ እንዳጠፋች ያውቁ ዘንድ አልቀለጡም። 23 ጻድቃንም ዳግመኛ ይህን በተመገቡ ጊዜ የራሳቸውን ምግብ ኀይል ይረሳሉ። 24 ፈጣሪ ሆይ፥ ፍጥረቱ ሁሉ ለአንተ ያገለግላልና፥ በዐመፀኞች ላይ የሚላክ ፍርድን ታመጣለህ፥ በአንተ ወደሚታመኑም ይደርስ ዘንድ ደስታን ትሰጣለህ። 25 ስለዚህም ያንጊዜ ስጦታህ ነበረች፥ ወደ ሥራውም ሁሉ ትለዋወጥ ነበር፤ በለመኑትና በወደዱትም ምግብ ሁሉ ታገለግል ነበር። 26 አቤቱ በአንተ ያመኑ ሰዎችን ቃልህ ይጠብቃቸዋል እንጂ፥ ሰው የሚመገበው የተለያየ የዘር ፍሬ እንዳይደለ የወደድኻቸው ልጆችህ ያውቁ ዘንድ ነው። 27 እሳት የማያጠፋው መና በጥቂት የፀሐይ ሙቀት ሞቆ ቀልጧልና። 28 በፀሐይ መውጫ በኩል አንተን እናመሰግን ዘንድ፥ ወዳንተም እንለምን ዘንድ ፀሐይ ወደ እኛ እንዲመጣ ይፈለጋልና ይህ ይታወቅ ዘንድ ነው። 29 ለማያመሰግን አለኝታው እንደ ክረምት ውርጭ ይቀልጣልና፥ እንደማይረባ ርኩስ ውኃም ይፈስሳልና። |