La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


መጽሐፈ ዮዲት 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ዮዲት 14

ድል አይሁዶች የአሦራውያንን ሰፈር አጠቁ

1 ዮዲትም እንዲህ አለቻቸው፦ “ወንድሞቼ ስሙኝ፥ ይህን ራስ ውሰዱና በግንቡ ላይ ስቀሉት።

2 ጧት ሲነጋና በምድር ላር ፀሐይ ስትወጣ ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፤ ለጦር የደረሱ ወንዶች ሁሉ ከከተማይቱ ይውጡ፤ አንድ አለቃ ሹሙ፥ ወደ አሦራውያን ሜዳው የጥበቃ ኬላ የምትወርዱ ምሰሉ፤ ነገር ግን አትውረዱ።

3 የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ወደ ጦር ሰፈራቸው ይሄዳሉ፤ የአሦርን የጦር ሠራዊት አዛዦችን ይቀሰቅሳሉ፤ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን ይሮጣሉ፥ ነገር ግን አያገኙትም። በዚያን ጊዜ ፍርሃት ይይዛቸዋል፥ ከፊታችሁም ይሸሻሉ።

4 እናንተና በእስራኤል ዙሪያ የሚኖሩ ሁሉ ተከተሏቸው፥ በመንገዳቸውም ላይ ምቱአቸው።

5 ይህን ከማድረጋችሁ በፊት ግን የእስራኤልን ቤት የናቀውንና ከእኛም ጋር እንዲሞት ወደ እኛ የላከውን ሰው እንዲያይና እንዲለይና አሞናዊውን አኪዮርን ጥሩልኝ።”

6 አኪዮርን ከዑዚያ ቤት ጠሩት፤ መጥቶም በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ከነበሩት ውስጥ አንድ ሰው የሆሎፎርኒስን ራስ በእጁ ይዞ ባየ ጊዜ በግንባሩ ተደፋ፥ መንፈሱም ከዳው።

7 በአነሡትም ጊዜ በዮዲት እግር ሥር ወደቀ፤ ሰገደላትም፥ እንዲህም አለ “በይሁዳ ድንኳኖች ሁሉ የተባረክሽ ነሽ፤ ስምሽን የሚሰሙ አሕዛብ ሁሉ ይሸበራሉ።

8 አሁንም በእነዚህ ቀኖች ያደረግሽውን ሁሉ እስቲ ንገሪኝ።” ዮዲትም ከወጣችበት ቀን ጀምሮ አሁን ንግግር እስከምታደርግበት ጊዜ ድረስ ያደረገችውን ሁሉ በሕዝቡ መካከል አወራችለት።

9 ንግግርዋን በጨረሰች ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ በከተማቸውም የደስታ ጩኸት ጮኹ።

10 አኪዮርም የእስራኤል አምላክ ያደረገውን ሁሉ በአየ ጊዜ ፈጽሞ በእግዚአብሔር አመነ። ሸለፈቱን ተገርዞ የእስራኤልን ቤት ተቀላቀለ፥ እስከ ዛሬ ድረስም አለ።

11 በነጋም ጊዜ የሆሎፎርኒስን ራስ በግንቡ ላይ ሰቀሉት፤ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣርያውን ይዞ ሁሉም በጭፍራቸው ሆነው ወደ ተራራው መውረጃ ወጡ።

12 የአሦር ልጆችም በአዩአቸው ጊዜ ወደ አለቆቻቸው፥ አለቆቻቸውም ወደ ጦር መሪዎቻቸው፥ ወደ አዛዦቻቸውና ገዢዎቻቸው ሰው ላኩ።

13 ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን መጥተው የግሉ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነውን “ጌታችንን ቀስቅስልን፥ ባሮቹ እስከ መጨረሻው ሊጠፉ ፈልገው ከእኛ ጋር ሊዋጉ ወደዚህ መውረድን ደፍረዋል” አሉት።

14 ባጎስም የድንኳኑን በር አንኳኳ፥ ከዮዲት ጋር የተኛ መስሎት ነበርና።

15 ነገር ግን የሚሰማው ሲያጣ፥ ገልጦ ወደ መኝታ ቤቱ ገባ፤ ሬሳው መሬት ላይ ወድቆ፥ አንገቱም ተቆርጦ ተወስዶ አገኘው።

16 በታላቅ ድምፅ በጣም ጮኸ፥ አለቀሰ፥ አቃሰተ፥ ጮኸ፥ ልብሱንም ቀደደ።

17 ዮዲት ወደነበረችበት ድንኳን ገባ፥ አላገኛትምም፥ ወደ ሕዝቡ እየተጣደፈ ወጣና እንዲህ ሲል ጮኸ፦

18 “ባሮቹ አታልለውናል፤ አንዲት ዕብራዊት ሴት የንጉሥ ናቡከደነፆርን ቤት ኀፍረት አከናንባዋለች፤ የሆሎፎርኒስ ሬሣ መሬት ላይ ወድቋል፥ ራሱም በላዩ የለም።”

19 የአሦር ጦር ሠራዊት አለቆች ይህንን ቃል በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ነፍሳቸውም በጣም ታወከች፥ ታላቁ ጩኸታቸውና ለቅሶአቸው በጦር ሰፈሩ አስተጋባ።