Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዮዲት 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 በመሸም ጊዜ ባርያዎቹ ተጣድፈው ወጡ፤ ባጎስም ድንኳኑን ከውጭ ዘጋ፥ በጌታው ፊት ያሉ አሽከሮችንም አስወጣቸው፤ ብዙ ጠጥተው ሁሉም ተዳከመው ነበርና ወደ ማደሪያቸው ገቡ። 2 ነገር ግን ዮዲት ብቻዋን ከሆሎፎርኒስ ጋር በድንኳኑ ቀረች፥ እርሱ በወይን በጣም ሰክሮ በአልጋው ላይ ተኝቶ ነበር። 3 ዮዲት አገልጋይዋን ሌላ ጊዜ እንደምታደርገው እስክትወጣ ድረስ ከመኝታ ቤቱ ውጭ ቆማ እንድትጠብቃት ነገረቻት፤ ለጸሎቷ እንደምትወጣ ነግራታለችና፤ ለባጎስም ይህንኑ ነገረችው። 4 ሁሉም ከፊትዋ ወጡ፥ ከትንሽ እስከ ትልቅ ማንም በመኝታ ቤቱ የቀረ አልነበረም። ዮዲት በአልጋው አጠገብ ቆመች፥ በልቧም እንዲህ አለች፦ “የኃይል ሁሉ አምላክ ጌታ ሆይ ስለ ኢየሩሳሌም ክብር በዚች ሰዓት በእጄ የማደርገውን ስራ ተመልከት። 5 ርስትህን ለመርዳትና በእኛ ላይ የተነሱብንን ጠላቶቻትንን ለማጥፋት ጊዜው አሁን ነው።” 6 በሆሎፎርኒስ ራስ አጠገብ ወዳለው ራስጌ ሄደች፥ ከዛው ሰይፉን መዘዘች። 7 ወደ አልጋው ተጠጋች፥ የራሱንም ጠጉር ይዛ “የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፥ ዛሬ አበርታኝ” አለች። 8 በኃይሏ ሁለት ጊዜ አንገቱን መታችው፥ አንገቱን ቆረጠችው። 9 ሬሳውን ከአልጋው አንከባለለችው፥ መጋረጃውን ከምሰሶው አወረደች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወጥታ ለአገልጋይዋ የሆሎፎርኒስን ራስ ሰጠቻት፥ 10 እህል በምትይዝበት ከረጢቷ ከተተችው፤ እንደተለመደው ለጸሎት እንደሚሄዱ ሁለቱም አብረው ወጡ፤ ሰፈሩን አቋርጠው ሸለቆውን ዞረው ወደ ቤቱሊያ ተራራ ወጡ፤ ወደ በሮቿም ደረሱ፤ ዮዲት የሆሎፎርኒስን ጭንቅላት ይዛ ወደ ቤጤልዋ ሄደች 11 ዮዲትም በሩቅ ሆና በር የሚጠብቁትን ዘበኞች፦ “ክፈቱ፥ በሩን ክፈቱ፥ ዛሬ እንዳደረገው ሁሉ ኃይሉን በእስራኤል ላይ ብርታቱንም በጠላቶቻችን ላይ ያሳይ ዘንድ አምላካችን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” አለቻቸው። 12 የከተማይቱ ሰዎች ድምጿን በሰሙ ጊዜ ወደ ከተማቸው በር ፈጥነው ወረዱ፥ የከተማይቱን ሽማግሌዎች ጠሩ። 13 መመለሷ የማይታሰብ ነበርና ከትልቁ እስከ ትንሹ ሁሉም እየሮጡ መጡ። በሩንም ከፍተው ተቀበሏቸው፤ ብርሃን እንዲሆን እሳት አንድደው ዙሪያቸውን ከበቡአቸው። 14 እርሷም በታላቅ ድምፅ “እግዚአብሔርን አመስግኑት፥ አመስግኑት፥ ምሕረቱን ከእስራኤል ቤት ያላረቀ፥ ነገር ግን ዛሬ በዚህች ሌሊት ጠላቶቻችንን በእኔ እጅ ያጠፋ እግዚአብሔርን አመስግኑ” አለቻቸው። 15 ራሱንም ከከረጢቱ አውጥታ አሳየቻቸው፤ እንዲህም አለች፦ “የአሦር ሠራዊት ዋና የጦር አዛዥ የሆሎፎርኒስ ራስ ይኸውላሁ፤ ሰክሮ በተኛበት ቦታ የተጋረደው መጋረጃም ይኸውላችሁ፤ ጌታ በሴት እጅ መታው። 16 በሄድሁበት መንገድ በጠበቀኝ በሕያው ጌታ እምላለሁ፥ ለገዛ ጥፋቱ ያማለለው ውበቴ ነበር፤ እኔን የሚሳድፍና የሚያሳፍር ኃጢአት ግን ከእኔ ጋር አልሠራም።” 17 ሕዝቡ ሁሉ እጅግ ተደነቁ፤ ሁሉም ሰግደው እግዚአብሔርን አመለኩ፥ በአንድ ድምጽም እንዲህ አሉ፦ “ዛሬ በዚህች ቀን የሕዝብህን ጠላቶች ያዋረድህ አምላካችን ቡሩክ ነህ።” 18 ዑዚያም እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በምድር ካሉ ሴቶች ሁሉ ይልቅ በልዑል እግዚአብሔር የተባረክሽ ነሽ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የጠላቶቻችን አለቃ አንገት ለመቁረጥ የመራሽ ጌታ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። 19 ተስፋሽ የእግዚአብሔርን ኃይል ከሚያስታውስ ሰው ልብ ምንጊዜም አይጥፋም። 20 አንቺ ሕዝባችን በመዋረዱ ምክንያት ለነፍስሽ ያልሳሳሽ፥ በአምላካችን ፊትም በቀጥታ መንገድ በመሄድ ጥፋታችንን የተከላከልሽ እግዚአብሔር ለዘለዓለም እንድትከብሪ ያድርግሽ፤ በመልካም ሥራዎችም ይጐብኝሽ።” ሕዝቡም ሁሉ፦ “ይሁን፥ ይሁን” አሉ። |