ዘዳግም 7:25 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ ከእነርሱም የተሠራባቸውን ብርንና ወርቅን፥ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትበድልበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ አትመኝ፥ በጌታ አምላካችሁም ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጣዖቶቻቸውን በእሳት አቃጥል፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ የራስህ ንብረት አድርገህ ለመውሰድ ልብህ አይመኝ፤ ይህን ብታደርግ ወጥመድ ይሆንብሃል፤ እግዚአብሔርም አምልኮ ጣዖትን ስለሚጠላ ብርቱ ጥፋትን ያስከትልብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። |
“የባልንጀራህን ሚስት፥ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ እርሻውንም፥ ሎሌውንም፥ ገረዱንም፥ በሬውንም፥ አህያውንም፥ ከብቱንም ሁሉ ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማንኛውንም አትመኝ።”
የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ ፈጨው፤ አደቀቀውም፤ በውኃም ላይ በተነው፤ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣቸው።
ሙሴም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ግብፃውያን እርም የሚሉትን እንሠዋለንና እንዲሁ ይሆን ዘንድ አይቻልም፤ እነሆ፥ ግብፃውያን እርም የሚሉትን እኛ በፊታቸው ብንሠዋ በድንጋይ ይወግሩናል።
በብርም ወደ ተለበጡ፥ በወርቅም ወደ አጌጡ ወደ ጣዖታቱ እንሂድ የሚሉ ናቸው፤ ያንጊዜ እንደ ትቢያ የደቀቁ ይሆናሉ፤ እንደ ውኃም ይደፈርሳሉ፤ በእነርሱም ጥራጊዎችን ይጥሉባቸዋል።
ልብሱን ያቃጥላል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን ወይም ከቆዳ የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠላል።
ጣዖታትንም አትከተሉ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፣ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፣ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐጸዶቻቸውንም ቁረጡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ምስሎች በእሳት አቃጥሉ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ።
ዕቃዋንም ሁሉ ወደ አደባባይዋ ትሰበስባለህ፤ ከተማይቱንም፥ ዕቃዋንም ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት በእሳት ፈጽመህ ታቃጥላለህ፤ ለዘለዓለምም ወና ትሆናለች፤ ደግሞም አትሠራም።
“በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ።
ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የአመንዝራዪቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።
“በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን፥ የተቀረፀ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ።
አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የአሕዛብ ምርኮ ትበላለህ፤ ዐይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ለአንተ ክፉ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው።
ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የአማልክቶቻቸውንም ምስል በእሳት አቃጥሉ።
የእስራኤል ልጆች ግን እርም በሆነው ነገር ታላቅ በደል በደሉ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነ አካን፥ እርሱም የከርሚ ልጅ፥ የዘንበሪ ልጅ፥ የዛራ ልጅ እርም ከሆነው ነገር ወሰደ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች ላይ ተቈጣ።
በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ ካባ፥ ሁለት መቶ ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፤ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፤ ብሩም ከሁሉ በታች ነው” አለው።