ዘሌዋውያን 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የለምጽ ደዌ ሕግ 1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 2 “ሰው በሥጋው ቆዳ ላይ እባጭ ብትወጣበት፥ ብትነጣም፥ በሥጋውም ቆዳ እንደ ለምጽ ደዌ ብትመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆች ወደ አንዱ ያምጡት። 3 ካህኑም በሥጋው ቆዳ ያለችውን ያችን ደዌ ይያት፤ ጠጕሯም ተለውጣ ብትነጣ በሥጋው ቆዳ ያለች የዚያች ደዌ መልክ ቢከፋ፥ ደዌውም ወደ ሥጋው ቆዳ ቢጠልቅ፥ እርስዋ የለምጽ ደዌ ናት፤ ካህኑም አይቶ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይበለው። 4 ቋቍቻውም በሥጋው ቆዳ ላይ ቢነጣ፥ ከቆዳውም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 5 በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያችን ደዌ ይያት፤ እነሆም፥ ያች ደዌ በፊት እንደ ነበረች ብትሆን፥ በቆዳውም ላይ ባትሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይለየዋል። 6 ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ያች ደዌ ብትከስም፥ በቆዳውም ላይ ባትሰፋ፥ ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ምልክት ነውና፥ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 7 ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ ምልክቱ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ እንደገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። 8 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ምልክቱ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ለምጽ ነውና። 9 “የለምጽ ደዌ በሰው ላይ ቢወጣ እርሱ ወደ ካህኑ ይሄዳል። 10 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ በቆዳው ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ 11 እርሱ በሥጋው ቆዳ ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፤ ካህኑም፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና ይለየዋል። 12 ለምጹም በቆዳው ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቆዳውን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፤ 13 ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ለምጹ ቆዳውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው፦ ካህኑ ‘ንጹሕ ነህ’ ይለዋል፤ ሁለመናው ተለውጦ ነጭ ሆኖአልና ንጹሕ ነው። 14 ደዌው በታየበት ቀን ጤነኛው ቆዳ ርኩስ ይሆናል። 15 ካህኑም ጤነኛውን ቆዳ አይቶ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ስለዚህ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው። 16 ጤነኛው ቆዳ ተመልሶ ቢነጣ እንደገና ወደ ካህኑ ይመጣል። 17 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ንጹሕ ነውና። 18 “በሥጋውም ቆዳ ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥ 19 በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቍቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። 20 ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቆዳው ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል። 21 ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቆዳውም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። 22 በቆዳውም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ በእትራቱ ላይ ወጥቶአልና። 23 ያች ደዌ ግን በስፍራዋ ብትቆም፥ ባትሰፋም፥ የቍስል እትራት ናት፤ ካህኑም፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። 24 “በሥጋውም ቆዳ የእሳት ትኩሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ፥ ወይም ቀላ ያለ ቋቍቻ ቢታይ፥ 25 ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቆዳውም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነውና። 26 ካህኑም ቢያየው፥ በቋቍቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቆዳውም ባይጠልቅ፥ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይለየዋል። 27 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቆዳውም ላይ ቢሰፋ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነውና በእትራቱ ላይ ወጥቶአል። 28 ቋቍቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቆዳውም ላይ ባይሰፋ፥ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኩሳት እባጭ ነው፤ የትኩሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። 29 “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ የለምጽ ደዌ ቢኖርበት፥ ካህኑ የለምጹን ደዌ ያያል፤ 30 እነሆም፥ ወደ ቆዳው ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ፦ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው። 31 ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቆዳውም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይለየዋል። 32 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቆዳው ባይጠልቅ፤ ይላጫል፤ 33 ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈርቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይለየዋል። 34 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ከተላጨ በኋላ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቆዳው ባይጠልቅ፥ ካህኑ፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 35 ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤ 36 እነሆም፥ ቈረቈሩ በቆዳው ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነውና። 37 ቈረቈሩ ግን ፊት እንደ ነበረ በቦታው ቢኖር፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል፤ እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም፦ ‘ንጹሕ ነው’ ይለዋል። 38 “ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቆዳ ላይ ነጭ ቋቍቻ ቢኖርበት፥ 39 ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቆዳ ላይ ያለው ቋቍቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቆዳው ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው። 40 “የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 41 ጠጕሩ ከግንባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 42 በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ፥ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው። 43 ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት በሥጋው ቆዳ ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥ 44 ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ፦ በርግጥ ‘ርኩስ ነው’ ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው። 45 “የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፤ ራሱም የተገለጠ ይሁን፤ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ይባላል። 46 ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል። በልብስ ላይ ስለሚታይ የለምጽ ደዌ ምልክት ሕግ 47 “የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን፥ 48 በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን፥ ቆዳ ወይም ከቆዳ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥ 49 ደዌው በልብሱ ወይም በቆዳው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ያሳያል። 50 ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይለየዋል። 51 በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በቆዳው ወይም ከቆዳው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 52 ልብሱን ያቃጥላል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም የተልባ እግር ቢሆን ወይም ከቆዳ የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠላል። 53 “ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥ 54 ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ያዝዛል፤ ሌላም ሰባት ቀን ይለየዋል። 55 ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ፥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት ያቃጥሉታል፤ በልብሱም ውስጥ በማጉም፥ በድሩም ወጥቶአልና። 56 “ካህኑም ቢያይ፥ እነሆ፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከቆዳው ይቅደደው። 57 በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር ያቃጥሉት። 58 ልብሱ ወይም ድሩ ወይም ማጉ ወይም ከቆዳ የተደረገው ነገር ከታጠበ በኋላ ደዌው ቢለቅቀው ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 59 “በበግ ጠጕር ልብስ፥ ወይም በተልባ እግር ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከቆዳ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።” |