ዘዳግም 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና ነውር ወይም ክፉ ነገር ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አትሠዋ። 2 “አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ሀገሮች በአንዲትዋ ውስጥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን ቃል ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ክፋት የሠራ ቢገኝ፥ 3 ሄዶም ሌሎች አማልክትን ያመለከ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ላላዘዘህ ለፀሐይና ለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ ቢገኝ፥ 4 ቢያወሩልህም ብትሰማም፥ ያን ፈጽመህ መርምር፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ በእስራኤልም መካከል እንዲህ ያለ ርኵሰት እንደ ተሠራ ርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥ 5 ይህን ክፉ ነገር የሠሩትን ያን ወንድ ወይም ያችን ሴት ታወጣቸዋለህ፥ እስኪሞቱም ድረስ በድንጋይ ትመትዋቸዋላችሁ። 6 በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ሞት የሚገባቸው ይገደሉ፤ በአንድ ምስክር ግን አይገደሉ። 7 እርሱን ለመግደል በመጀመሪያ የምስክሮች እጅ በኋላም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ትሁንበት፤ እንዲሁ ክፉውን ከመካከላችሁ አስወግዱ። በካህናትና ዳኞች የሚሰጡ የፍርድ ውሳኔዎች 8 “በደምና በደም መካከል፥ በፍርድና በፍርድ መካከል፥ በመቍሰልና በመቍሰል መካከል፥ በክርክርና በክርክር መካከል በሀገርህ ውስጥ ሰዎች ስለሚከራከሩበት ክርክር የሚሳንህ የፍርድ ነገር ቢኖር፥ አንተ ተነሥተህ ስሙ በዚያ ይጠራ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትወጣለህ፤ 9 ወደ ሌዋውያን ካህናት በዚያም ዘመን ወደ አሉ ፈራጆች መጥተህ ትጠይቃለህ፤ እነርሱም የፍርዱን ነገር ይነግሩሃል። 10 ስሙ በዚያ ይጠራ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ እንደ ነገሩህ ቃል ታደርጋለህ፤ ያስተማሩህንም ሕጉን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 11 እንዳስተማሩህም ሕግ፥ እንደ ነገሩህም ፍርድ አድርግ፤ ከነገሩህ ፍርድ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። 12 ማናቸውም ሰው ቢኰራ፥ በአምላክህ እግዚአብሔር ስም ለማገልገል የሚቆመውን ካህኑን ወይም በዚያ ወራት ያለውን ፈራጁን ባይሰማ ያ ሰው ይሙት፤ ከእስራኤልም ዘንድ ክፉውን አስወግዱ፤ 13 ሕዝቡም ሁሉ ሰምቶ ይፈራል፤ ከዚያም ወዲያ ደግሞ አይበድልም። ስለ ንጉሥ የተሰጠ መመሪያ 14 “አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ፥ በወረስሃትም ጊዜ፥ በተቀመጥህባትም ጊዜ፦ በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ አለቃ እሾማለሁ ብትል፥ 15 ከወንድሞችህ መካከል አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን ለአንተ አለቃ ትሾማለህ፤ ወንድምህ ያልሆነውን ሌላ ሰው በአንተ ላይ መሾም አትችልም። 16 ለእርሱ ፈረሶችን እንዳያበዛ፥ ሕዝቡንም ወደ ግብፅ እንዳይመልስ፤ እግዚአብሔር፦ በዚያች መንገድ መመለስን አትድገም ብሎአልና። 17 ልቡም እንዳይስት ሚስቶችን ለእርሱ አያብዛ፤ ወርቅና ብርም ለእርሱ እጅግ አያብዛ። 18 “በግዛቱም በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሁለተኛ ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። 19 መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው። አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ፥ ይህችንም ሥርዐት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፥ 20 ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኰራ፥ የአምላኩ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንዳይተው፥ ቀኝና ግራም እንዳይል፥ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረዥም ዘመን ይገዙ ዘንድ። |