ዘፀአት 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)2፥ ጓጕንቸር 1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ፥ ሀገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤ 3 ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፤ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ሹሞችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ቡሃቃዎችህም፥ ወደ ምድጃዎችህም ይገባሉ፤ 4 ጓጕንቸሮችም በአንተ፥ በሕዝብህም፥ በሹሞችህም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።” 5 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወንድምህን አሮንን፦ ‘በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖዎቹ፥ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችንም አውጣ’ ” በለው። 6 አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፤ የግብፅንም ሀገር ሸፈኑ። 7 የግብፅ ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፤ በግብፅም ሀገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ። 8 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔ፥ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ” አላቸው። 9 ሙሴም ፈርዖንን፥ “ጓጕንቸሮቹ ከአንተ፥ ከሕዝብህም፥ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ፥ ለሹሞችህም፥ ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ ቅጠረኝ” አለው። ፈርዖንም፥ “ነገ” አለው። 10 ሙሴም፥ “ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እሺ እንደ አልህ ይሁን። 11 ጓጕንቸሮቹም ከአንተ፥ ከቤቶችህም፥ ከመንደሮችህም፥ ከሹሞችህም፥ ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ” አለው። 12 ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም ፈርዖን እንደ ቀጠረው ሰለ ጓጕንቸሮቹ መራቅ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13 እግዚአብሔርም ሙሴ እንደ አለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት፥ ከመንደርም፥ ከሜዳም ሞቱ። 14 እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች። 15 ፈርዖንም ጸጥታ እንደ ሆነ በአየ ጊዜ ልቡ ደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው አልሰማቸውም። 3፥ ቅማል 16 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “አሮንን፦ ‘በትርህን በእጅህ ዘርጋ፤ የምድሩንም ትቢያ ምታ’ በለው፤ ቅማልም በግብፅ ሀገር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ይወጣል።” 17 አሮንም እጁን ዘረጋ፤ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፤ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ ሀገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ። 18 የግብፅ ጠንቋዮችም በአስማታቸው ቅማል ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፤ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ። 19 ጠንቋዮችም ፈርዖንን፥ “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። 4፥ ተናካሽ ዝንብ 20 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ማልደህ ተነሣ፤ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ፥ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በምድረ በዳ እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21 ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ፥ በአንተ፥ በሹሞችህም፥ በሕዝብህም፥ በቤቶችህም ላይ የውሻ ዝንብ እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች፥ የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በውሻ ዝንብ ይመላሉ። 22 በዚያም ቀን የምድር ሁሉ አምላክ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የውሻ ዝንብ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ። 23 በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ነገር ነገ በምድሪቱ ላይ ይሆናል።” 24 እግዚአብሔርም እንዲህ አደረገ፤ የውሻው ዝንብም በፈርዖን ቤት፥ በሹሞቹም ቤቶች ውሰጥ፥ በግብፅም ሀገር ሁሉ መጣ፤ ምድሪቱም ከውሻው ዝንብ የተነሣ ጠፋች። 25 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ በዚያች ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው። 26 ሙሴም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችን ግብፃውያን እርም የሚሉትን እንሠዋለንና እንዲሁ ይሆን ዘንድ አይቻልም፤ እነሆ፥ ግብፃውያን እርም የሚሉትን እኛ በፊታቸው ብንሠዋ በድንጋይ ይወግሩናል። 27 እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እግዚአብሔር እንዳዘዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን” አለ። 28 ፈርዖንም፥ “ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን በጣም ርቃችሁ አትሂዱ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩልኝ” አለ። 29 ሙሴም፥ “እነሆ፥ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፤ ወደ እግዚአብሔርም እጸልያለሁ፤ የውሻ ዝንቡም ከአንተ፥ ከሹሞችህና ከሕዝብህ ነገ ይርቃል፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ሕዝቡን እንደማትለቅቅ እንደገና ማታለልን አትድገም።” 30 ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። 31 እግዚአብሔርም ሙሴ እንደ አለ አደረገ፤ የውሻውንም ዝንብ ከፈርዖን፥ ከሹሞቹም፥ ከሕዝቡም አራቀ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም። 32 ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም አልለቀቀም። |