ዘዳግም 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከእግዚአብሔር ጉባኤ የሚለይ ሁኔታ 1 “ፍሬ ዘሩ የተቀጠቀጠ፥ አባለ ዘሩም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ። 2 ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ፤ 3 “አሞናዊ ወይም ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ፤ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ ለዘለዓለም ወደ እግዚአብሔር ቤት አይግባ። 4 ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እንጀራና ውኃ ይዘው በመንገድ ላይ አልተቀበሉአችሁምና፥ ከመስጴጦምያ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግማችሁ ዘንድ ተዋውለውባችኋልና። 5 ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ወድዶሃልና ርግማኑን ወደ በረከት ለወጠልህ። 6 በዘመንህ ሁሉ ለዘለዓለም ሰላም እንደሚገባቸው አታናግራቸው። 7 “ኤዶማዊዉ ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፤ ግብፃዊዉንም በሀገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። 8 ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ቤት ይግቡ። ሰፈርን በንጽሕና መጠበቅ 9 “ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። 10 በእናንተ ውስጥ ሌሊት በሚሆነው ርኵሰት የረከሰ ሰው ቢኖር፥ ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፤ ወደ ሰፈርም አይግባ። 11 በመሸም ጊዜ ሰውነቱን በውኃ ይታጠብ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ። 12 ወደ ሜዳም ትወጣባት ዘንድ ከሰፈር ውጭ ቦታ ይኑርህ። 13 ከመሣርያህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ ሜዳም በተቀመጥህ ጊዜ ትምስበታለህ፤ ዞረህም ከአንተ የወጣውን በአፈር ትከድነዋለህ። 14 አምላክህ እግዚአብሔር ሊያድንህ፥ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥህ በሰፈርህ ውስጥ ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ፥ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሰፈርህ የተቀደሰ ይሁን። ልዩ ልዩ ሕግጋት 15 “ከጌታዉ ኰብልሎ ወደ አንተ የተጠጋውን ባሪያ ለጌታው አሳልፈህ አትስጥ። 16 ከአንተ ጋር ይኑር፤ በመካከልህም በሚወድዳት በአንዲቱ ስፍራ ይቀመጥ፤ አንተም አታስጨንቀው። 17 “ከእስራኤል ሴቶች ልጆች ሴት አመንዝራ አትገኝ፤ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች ወንድ አመንዝራ አይገኝ። 18 ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የአመንዝራዪቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና። 19 “ለወንድምህ በወለድ አታበድር፤ የብር ወይም የእህል፥ ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ። 20 ለእንግዳው በወለድ አበድር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ለወንድምህ በወለድ አታበድር። 21 “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኀጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘግይ። 22 ባትሳል ግን ኀጢአት የለብህም። 23 በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ። 24 “ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ፤ ወዳልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታግባ። 25 ወደ ባልንጀራህ የወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ፤ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አታግባ። |