ቈላስይስ 3:11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ፥ ግሪካዊም፥ የተገዘረ፥ ያልተገዘረም፥ አረመኔም፥ ባላገርም፥ ቤተ ሰብእና አሳዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው። |
እርሱም፥ “የያዕቆብን ነገዶች እንደገና እንድታስነሣ፥ ከእስራኤልም የተበተኑትን ወደ አባቶች ቃል ኪዳን እንድትመልስ ባርያዬ ትሆን ዘንድ ለአንተ እጅግ ታላቅ ነገር ነውና፥ እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” ይላል።
እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፤ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።
ጌታ ሆይ! አንተ ኀይሌና ረዳቴ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ነህ፤ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው፥ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር ለምንም የማይረባቸውን ጣዖትን ሠርተዋል” ይላሉ።
ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ፥ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንደ አሉ የሀገር ልጆች ይሆኑላችኋል፤ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።
በምድርም ላይ ለእኔ እዘራታለሁ፤ ይቅርታ የሌላትን ይቅር እላታለሁ፤ ያልተወደደች የነበረችውን እወድዳታለሁ፤ ሕዝቤም ያልሆነውን፥ “አንተ ሕዝቤ ነህ” እለዋለሁ፤ እርሱም፥ “አንተ ጌታዬና አምላኬ ነህ” ይለኛል።
ይኸውም የቀሩ ሰዎችንና ስሜም የተጠራባቸውን አሕዛብን ሁሉ ይፈልጉ ዘንድ ነው” ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር።
ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፥ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ።
በዚያም ቀን ብዙ አሕዛብ ወደ እግዚአብሔር ይጠጋሉ፥ ሕዝብም ይሆኑኛል፣ በመካከልሽም እኖራለሁ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ወደ አንቺ እንደ ላከኝ ታውቂአለሽ።
ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፣ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፣ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን።
እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና።
እኔ በእነርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው።
የቀሩት ሰዎችና ስሜም የተጠራባቸው አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ ይላል ይህን የሚያደርግ እግዚአብሔር፤
በዚያ የሚኖሩት አረማውያንም አዘኑልን፤ መልካም ነገርንም አደረጉልን፤ ከቍሩም ጽናትና ከዝናሙ ብዛት የተነሣ እሳት አንድደው እንድንሞቅ ሁላችንንም ሰበሰቡን።
አረማውያንም እፉኝቱ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል፤ ከባሕር እንኳ በደኅና ቢወጣም በሕይወት ይኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ አልተወውም” አሉ።
አይሁዳዊንና አረማዊን አልለየም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ እግዚአብሔር ባለጸጋ ስለሆነ ለለመነው ሁሉ ይበቃልና።
እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል፤ አይሁድ ብንሆን፥ አረማውያንም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና።
የቋንቋውን ትርጓሜ ካላወቅሁ እኔ ለሚያነጋግረኝ እንደ እንግዳ እሆንበታለሁ፤ የሚያነጋግረኝ እርሱም ለእኔ እንደ እንግዳ ይሆናል።
ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ።
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና።
አሕዛብን ወራሾቹና አካሉ ያደርጋቸው ዘንድ፥ በወንጌልም ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ተስፋ አንድ ይሆኑ ዘንድ።
የእግዚአብሔርም ልጅ እንደ መጣ፥ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።