ሐዋርያት ሥራ 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጳውሎስ በመላጥያ ደሴት 1 ከዚህም በኋላ በደኅና በደረስን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባል ዐወቅን። 2 በዚያ የሚኖሩት አረማውያንም አዘኑልን፤ መልካም ነገርንም አደረጉልን፤ ከቍሩም ጽናትና ከዝናሙ ብዛት የተነሣ እሳት አንድደው እንድንሞቅ ሁላችንንም ሰበሰቡን። 3 ጳውሎስም ብዙ ጭራሮ ሰብስቦ በእሳቱ ላይ ጨመረው፤ እፉኝትም ከእሳቱ ወላፈን የተነሣ ወጥታ ጳውሎስን እጁን ነደፈችው። 4 አረማውያንም እፉኝቱ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል፤ ከባሕር እንኳ በደኅና ቢወጣም በሕይወት ይኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ አልተወውም” አሉ። 5 ጳውሎስ ግን እጁን አራግፎ እፉኝቱን በእሳት ውስጥ ጣላት፤ ጕዳትም አላገኘውም። 6 እነርሱ ግን ወዲያውኑ የሚያብጥ ወይም ሞቶ የሚወድቅ መስሎአቸው ነበር። እያዩትም ብዙ ሰዓት ቆሙ፤ አንዳችም እንደ አልጐዳው በአዩ ጊዜም፥ “ይህስ አምላክ ነው” ብለው ቃላቸውን ለወጡ። 7 በዚያ ቦታም አጠገብ ስሙን ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴቲቱ አለቃ መሬት ነበር፤ እርሱም ሦስት ቀን ሙሉ በደስታ በቤቱ ተቀብሎ አስተናገደን። 8 የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ይኖር ነበር፤ ጳውሎስም እርሱ ወዳለበት ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። 9 ያደረገውንም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ በዚያች ደሴት ያሉትን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ፈወሳቸውም። 10 እጅግ ታላቅ ክብርም አከበሩን፤ ከእነርሱም ዘንድ ለመሄድ በተነሣን ጊዜ የሚያስፈልገንን ስንቅ ሰጡን። ከመላጥያ ወደ ሮም ስለ መጓዛቸው 11 ከሦስት ወር በኋላም በዚያች ደሴት ወደ ከረመችው ወደ እስክንድርያ መርከብ ወጣን፤ በዚያች መርከብ ላይም የዲዮስቆሮስ ምልክት ነበረባት፤ ይኸውም “የመርከበኞች አምላክ” የሚሉት ነው። 12 ከዚያም ሄደን ወደ ሰራኩስ ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን። 13 ከዚያም ሄደን ሬቅዩን ወደምትባል ሀገር ደረስን፤ በማግሥቱም ወጣን፤ ከአንድ ቀንም በኋላ ከጐንዋ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ደረስን። 14 በዚያም ወንድሞችን አግኝተን ተቀበሉን፤ በእነርሱ ዘንድም ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ሄደን ወደ ሮሜ ደረስን። 15 በዚያም ያሉት ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ፤ አፍዩስ ፋሩስ እስከሚባለው ገበያና እስከ ሦስተኛው ማረፊያ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። 16 ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ የመቶ አለቃው እስረኞችን ለሠራዊቱ አለቃ አስረከበ፤ ጳውሎስ ግን ከሚጠብቀው አንድ ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት። ጳውሎስ ከአይሁድ ሊቃውንት ጋር ስለ መነጋገሩ 17 ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች ሰበሰባቸው፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ በሕዝቡም ላይ ቢሆን፥ በአባቶቻችንም ሕግ ላይ ቢሆን ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ ለሮም ሰዎች አሳልፈው ሰጡኝ። 18 እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስለአላገኙብኝ ሊፈቱኝ ወደዱ። 19 አይሁድ ግን ሊቃወሙኝ በተነሡ ጊዜ ወደ ቄሣር ይግባኝ ለማለት ግድ ሆነብኝ፤ ነገር ግን ወገኖችን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። 20 ስለዚህም ላያችሁ፥ ልነግራችሁና ላስረዳችሁ ወደ እኔ እንድትመጡ ማለድኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ በዚህ ሰንሰለት ታስሬአለሁና።” 21 የአይሁድ ታላላቅ ሰዎችም እንዲህ አሉት፥ “ለእኛስ ከይሁዳ ሀገር ስለ አንተ መልእክት አልደረሰንም፤ ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞችም ቢሆን አንድ ስንኳ ከዚህ አስቀድሞ ስለ አንተ ክፉ ነገር ያወራን፥ የነገረንም የለም። 22 ነገር ግን በዚህ ነገር በየስፍራው ሁሉ እንዲጣሉ በእኛ ዘንድ ታውቋልና የአንተን ዐሳብ ደግሞ ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንወድዳለን።” 23 ከዚህም በኋላ ወደ እርሱ የሚመጡበትን ቀን ቀጠሩትና ብዙዎች ወዳረፈበት ወደ እርሱ መጡ፤ ከጥዋትም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት እየጠቀሰ ነገራቸው። 24 ከእነርሱም እኩሌቶቹ የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አልተቀበሉትም። 25 እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ከእርሱ ተመለሱ፤ እንዲህም አላቸው፥ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት ለአባቶቻችን በእውነት እንዲህ ብሎ መልካም ነገር ተናግሮአል። 26 ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና እንዲህ በላቸው፦ መስማትን ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ግን አትመለከቱም። 27 በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ወደ እኔም እንዳይመለሱና ይቅር እንዳልላቸው የዚህ ሕዝብ ልባቸው ደንድኖአልና፥ ጆሮአቸውም ደንቁሮአልና፥ ዐይናቸውንም ጨፍነዋልና’። 28 እንግዲህ ከእግዚአብሔር የተገኘች ይህቺ ድኅነት ለአሕዛብ እንደምትሆን ዕወቁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።” 29 ይህንም በተናገራቸው ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ወጥተው ሄዱ። 30 ጳውሎስም በገንዘቡ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጣውንም ሁሉ ይቀበል ነበር። 31 ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብክ ነበር፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር። 32 ጳውሎስም በመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኔሮን ቄሣር ገብቶ ነበርና ረትቶ በሰላም ሄደ፤ ከዚህም በኋላ ሁለት ዓመት ኖሮ ከሮም ወጣ። 33 ከዚህም በኋላ ወደ ሮም ተመልሶ የኔሮን ቄሣር ዘመዶችን አጠመቀ፤ በኔሮን ትእዛዝም በሰይፍ ተመትቶ መከራውንም ታግሦ ሰማዕት ሆነ። ወንጌላዊው ሉቃስ የጻፈው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተፈጸመ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን። |