ገላትያ 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ቅዱስ ጳውሎስ ሁለተኛ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መውጣቱ 1 ከዐሥራ አራት ዓመትም በኋላ ከበርናባስ ጋር እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ቲቶንም ይዠው ሄድሁ። 2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ በከንቱ እንዳልሮጥ፥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆነ፥ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አለቆች መስለው ለሚታዩት አስታወቅኋቸው። 3 አብሮኝ የነበረው ቲቶም አረማዊ ሲሆን እንዲገዘር ግድ አላልሁትም። 4 ይኸውም ባሪያዎች ያደርጉን ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘናትን ነጻነት ሊሰልሉ በስውር ወደ እኛ የገቡ ሐሰተኞች መምህራንን ደስ አይበላቸው ብዬ ነው። 5 ለምንም ይሆናሉ ብለን የማናስባቸው ናቸው፤ እውነተኛው ትምህርት በእናንተ ይጸና ዘንድ አንዲት ሰዓትም እንኳ አልተገዛንላቸውም። 6 አለቆች የመሰሉት ግን ቀድሞ እነርሱ እንዴት እንደ ነበሩ ልናገር አያገደኝም፤ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና፤ አለቆች የመሰሉትም ከራሳቸው ምንም ነገር የጨመሩልኝ የለምና። 7 የጴጥሮስ ትምህርት በተገዘሩ በአይሁድ ዘንድ እንደ ታመነለት፥ የእኔም ትምህርት ባልተገዘሩ በአሕዛብ ዘንድ እንደ ታመነ ዐውቀዋል እንጂ። 8 ወደ ተገዘሩ አይሁድ በተላከ ጊዜ ጴጥሮስን የረዳው እርሱ እኔንም ባልተገዘሩ አሕዛብ ዘንድ ረዳኝ። 9 የሰጠኝንም ጸጋ ዐውቀው አዕማድ የሚሏቸው ያዕቆብና ኬፋ፥ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ፥ እነርሱም ወደ አይሁድ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን። 10 ይልቁንም ነዳያንን እንድናስባቸው ነው፤ ስለዚህም ይህን ነገር ልፈጽመው ተጋሁ። ጳውሎስ ጴጥሮስን ስለ መቃወሙ 11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፤ ነቅፈውት ነበርና። 12 ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፥ ከአረማውያን ጋር ይበላ ነበርና፥ በመጡ ጊዜ ግን ተለያቸው፤ ከአይሁድ ወገን የሆኑትን ፈርቶአልና። 13 ከአይሁድ ወገንም ወደዚህ ግብር የተመለሱ ብዙዎች ነበሩ፤ በርናባስም እንኳ በግብዝነታቸው ተባበረ። 14 ነገር ግን ወደ እውነተኛው ወንጌል እግራቸውን እንዳላቀኑ ባየሁ ጊዜ፥ በሰው ሁሉ ፊት ኬፋን እንዲህ አልሁት፥ “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን በአይሁድ ሥርዐት ያይደለ፥ በአረማውያን ሥርዐት የምትኖር ከሆነ እንግዲህ አይሁድ እንዲሆኑ አረማውያንን ለምን ታስገድዳቸዋለህ?” 15 እኛ በትውልዳችን አይሁድ ነን፤ ኀጢአተኞች የሆኑ አሕዛብም አይደለንም። 16 ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንደማይጸድቅ እናውቃለንና፤ እኛም የኦሪትን ሥራ በመሥራት ሳይሆን በእርሱ በማመናችን እንጸድቅ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነናል፤ ሰው ሁሉ በኦሪት ሥራ አይጸድቅምና። 17 በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንሻ እኛ እንደ ኀጢአተኞች ከሆን እንግዲህ ክርስቶስ የኀጢአት አገልጋይ መሆኑ ነውን? አይደለም። 18 ያን ያፈረስሁትን መልሼ የማንጽ ከሆነ ራሴን ሕግ አፍራሽ አደረግሁ። 19 እኔስ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ በሁለተኛው ሕግ እኖር ዘንድ ከቀደመው ሕግ ተለየሁ። 20 ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ። 21 የእግዚአብሔርንም ጸጋ አልክድም፤ የኦሪትን ሥራ በመሥራት የሚጸድቁ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ። |