ኤፌሶን 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እናንተም በኀጢአታችሁ ምውታን ሆናችሁ ነበር። 2 ይኸውም ቀድሞ በዚህ ዓለም ሥርዐት፥ አሁን በከሓድያን ልጆች የሚበረታታባቸውና፥ በነፋስ አምሳል የሚገዛቸው አለቃ እንደ ነበረው ፈቃድ ጸንታችሁ የነበራችሁበት ነው። 3 እኛ ሁላችን ቀድሞ እንደ ሥጋችን ምኞት ኖርን፤ የሥጋችንንም ፈቃድና ያሰብነውን አደረግን፤ እንደ ሌሎች ኃጥአንም ሁሉ የጥፋት ልጆች ሆንን። 4 እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጸግነትና በወደደን በፍቅሩ ብዛት፥ 5 በኃጢአታችን የሞትን ሳለን በክርስቶስ ሕይወትን ሰጠን፤ በጸጋውም ዳንን። 6 በኢየሱስ ክርስቶስም አስነሥቶ በሰማያት ከእርሱ ጋር አኖረን። 7 በኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ስላለን የጸጋውን ባለጠግነት ብዛት በሚመጣው ዓለም ይገልጥ ዘንድ፥ 8 አምነን በጸጋው ድነናልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ የእናንተ ሥራ አይደለም። 9 የሚመካም እንዳይኖር በምግባራችን አይደለም። 10 እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ላዘጋጀው በጎ ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ የፈጠረን ፍጥረቱ ነንና። ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላም 11 እናንተ አሕዛብ አስቡ፤ ቀድሞ በሥጋ ሥርዐት ነበራችሁ፤ ያልተገዘሩም ይሉአችሁ ነበር፤ እንዲህ የሚሉአችሁም የተገዘሩ ሰዎች ናቸው፤ ግዝረት ግን በሥጋ ላይ የሚደረግ የሰው እጅ ሥራ ነው። 12 ያንጊዜ ክርስቶስን አታውቁትም ነበር፤ ከእስራኤል ሕግ የተለያችሁ ነበራችሁ፤ ከተስፋው ሥርዐትም እንግዶች ነበራችሁ፤ ተስፋም አልነበራችሁም፤ በዚህም ዓለም እግዚአብሔርን አታውቁትም ነበር። 13 አሁን ግን ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀረባችሁ። 14 ሁለቱን አንድ ያደረገ ሰላማችን እርሱ ነውና፥ በሥጋውም በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ጥልን ሻረ። 15 ሁለቱንም አድሶ አንድ ያደርጋቸው ዘንድ በሥርዐቱ የትእዛዝን ሕግ አጠፋ፤ ዕርቅንም አደረገ። 16 በመስቀሉም በአንድ ሥጋው ሁለቱን ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ በእርሱም ጥልን አጠፋ። 17 መጥቶም፤ ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን። 18 እርሱ መርቶናልና፤ ሁለታችንንም በመንፈስ ቅዱስ ወደ አባቱ አቅርቦናልና። 19 እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። 20 በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልና የሕንጻው የማዕዘን ራስ ድንጋይም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ 21 እርሱም ሕንጻ ሁሉ የሚያያዝበት፥ የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ግንብ የሚያድግበት ነው። 22 እናንተ በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ልትሆኑ በእርሱ ታነጻችሁ። |