ዮሐንስ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እምነት 1 “ልባችሁ አይደንግጥ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ። 2 በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ እላችሁ ነበር። 3 ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተም እኔ በአለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔ እወስዳችኋለሁ። 4 ወዴትም እንደምሄድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” 5 ቶማስም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ የምትሄድበትን የማናውቅ እንግዲህ መንገዱን እንዴት እናውቃለን?” አለው። 6 ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7 እኔንስ ብታውቁኝ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን አውቃችሁታል፤ አይታችሁትማል።” 8 ፊልጶስም፥ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። 9 ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው፥ “ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን አብሬአችሁ ስኖር አታወቀኝምን? እኔን ያየ አብን አየ፤ እንግዲህ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ? 10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርሁት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ። 11 እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ። 12 “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን ሥራ እርሱም ይሠራል፤ ከዚያም የሚበልጥ ይሠራል፤ እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና። 13 አብ በወልድ ይከብር ዘንድ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ። 14 በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ያን አደርግላችኋለሁ። ስለ ጰራቅሊጦስ 15 “ከወደዳችሁኝስ ትእዛዜን ጠብቁ። 16 እኔም አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ ይልክላችኋል። 17 እርሱም ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ ይኖራልና፤ ያድርባችሁማልና። 18 “የሙት ልጆች ትሆኑ ዘንድ አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19 ገና ጥቂት ጊዜ አለ፤ እንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና፤ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20 እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ፥ እናንተም በእኔ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ ያንጊዜ ታውቃላችሁ። 21 ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለ የሚጠብቀውም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” 22 የአስቆሮቱ ሰው ያይደለ ይሁዳም፥ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ያይደለ ለእኛ ራስህን ትገልጥ ዘንድ እንዳለህ የተናገርኸው ምንድን ነው?” አለው። 23 ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን። 24 የማይወደኝ ግን ቃሌን አይጠብቅም፤ ይህም የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ቃል ነው እንጂ የእኔ ቃል አይደለም። 25 “ከእናንተም ጋር ሳለሁ ይህን ነገርኋችሁ። 26 ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። ስለ ሰላም 27 “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፤ አትፍሩም። 28 እኔ እንደምሄድ ወደ እናንተም እንደምመለስ የነገርኋችሁን ሰምታችኋል፤ ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ እርሱ አብ ይበልጠኛልና። 29 አሁንም ይህ በሆነ ጊዜ ታምኑ ዘንድ አስቀድሜ ሳይሆን ነገርኋችሁ። 30 እንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፤ የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና፤ በእኔም ላይ ምንም አያገኝም። 31 ነገር ግን አብን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ አብ ትእዛዙን እንደ ሰጠኝ እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ተነሡ ከዚህ፤ እንሂድ። |