2 ነገሥት 22:13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ ስለዚችም ስለተገኘችው መጽሐፍ ቃል ሁሉ እግዚአብሔርን ጠይቁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የነደደው የእግዚአብሔር ቍጣ ታላቅ ነውና።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቆጥቶአል።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እንግዲህ ሂዱና እኔና የይሁዳ ነዋሪ ሕዝብ በዚህ በተገኘው መጽሐፍ ስላለው ትምህርት ማወቅ እንችል ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ የቀድሞ አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መመሪያ ስላልተከተሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በጣም ተቈጥቶአል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) “አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ የዚህችን የተገኘችውን መጽሐፍ ቃል እግዚአብሔርን ጠይቁ፤” ብሎ አዘዛቸው። |
ኢዮሣፍጥም፥ “በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮች አንዱ፥ “ኤልያስን እጁን ያስታጥብ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ” ብሎ መለሰ።
አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ርቀዋል፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ረስተዋል፤ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር ቤት መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም አዙረዋል፤
“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ስለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ስለቀሩትም እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው።
በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ለእግዚአብሔርም ተናዘዙ፤ ለአምላካቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኀጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤
ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ታላቅ ቍጣን ተቈጣ፤ እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፤ ሬሳቸውም በመንገድ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ ፍላጎት ሄዳችኋል፤ እኔንም አልሰማችሁም።
እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትደርስ ይሆናል፤ ሁሉም ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”
ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ፥ “በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን?” ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም፥ “አዎን አለ፤ ደግሞም በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ” አለው።
ነገር ግን እኛና አባቶቻችን፥ ነገሥታቶቻችንም፥ አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ እናደርገው እንደ ነበረ፥ ለሰማይ ንግሥት እናጥን ዘንድ፥ የመጠጥንም ቍርባን እናፈስስላት ዘንድ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያ ጊዜም እንጀራን እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ነበር፤ ክፉም አናይም ነበር።