2 ነገሥት 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በሞዓባውያንና በእስራኤላውያን መካከል የተደረገ ጦርነት 1 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመተ መንግሥት የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ ዐሥራ ሁለትም ዓመት ነገሠ። 2 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ ነገር ግን እንደ አባቱና እንደ እናቱ አልነበረም፤ አባቱም ያሠራውን የበዓልን ምስል አጠፋ። 3 ነገር ግን እስራኤልን ያሳታቸውን የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት ተከተለ፤ እርሱንም አልተወም። 4 የሞዓብም ንጉሥ ሞሳ ባለ በጎች ነበር፤ ለእስራኤልም ንጉሥ መቶ ሺህ የጠጕር አውራ በጎችንና መቶ ሺህ ጠቦቶችን ይገብርለት ነበር። 5 አክዓብም ከሞተ በኋላ የሞዓብ ንጉሥ የእስራኤልን ንጉሥ ከዳው። 6 በዚያም ጊዜ ንጉሡ ኢዮራም ከሰማርያ ወጥቶ እስራኤልን ሁሉ ቈጠራቸው። 7 ወደ ይሁዳም ንጉሥ ወደ ኢዮሣፍጥ፥ “የሞዓብ ንጉሥ ከዳኝ፤ ከእኔ ጋር በሞዓብ ላይ ለሰልፍ ትሄዳለህን?” ብሎ፤ ላከ። እርሱም፥ “እወጣለሁ፤ እኔ እንደ አንተ፥ አንተም እንደ እኔ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለ። 8 ደግሞም፥ “በየትኛው መንገድ እንሄዳለን?” አለ፤ እርሱም፥ “በኤዶምያስ ምድረ በዳ መንገድ” አለው። 9 የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ፥ የኤዶምያስም ንጉሥ ሄዱ፤ የሰባትም ቀን መንገድ ዞሩ፤ ለሠራዊቱና ለሚጫኑ እንስሶች ውኃ አጡ። 10 የእስራኤልም ንጉሥ፥ “እግዚአብሔር በሞዓብ እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ እነዚህን ሦስቱን ነገሥታት ጠርቶአልና ወዮ!” አለ። 11 ኢዮሣፍጥም፥ “በእርሱ እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለ። ከእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮች አንዱ፥ “ኤልያስን እጁን ያስታጥብ የነበረው የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ እዚህ አለ” ብሎ መለሰ። 12 ኢዮሣፍጥም፥ “የእግዚአብሔር ቃል በእርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ የኤዶምያስም ንጉሥ ወደ እርሱ ወረዱ። 13 ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ወደ አባትህ ነቢያትና ወደ እናትህ ነቢያት ሂድ፥” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ፥ “አይደለም፤ በሞዓብ እጅ ይጥላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እነዚህን ሦስት ነገሥታት ጠርቶአልን?” አለው። 14 ኤልሳዕም፥ “በፊቱ የቆምሁት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን! የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ያፈርሁ ባልሆን ኖሮ አንተን ባልተመለከትሁና ባላየሁ ነበር። 15 አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ” አለ። ባለ በገናውም በደረደረ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ መጣ። 16 እንዲህም አለ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቈፍሩ። 17 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፤ ዝናብም አታዩም፤ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም፥ ከብቶቻችሁም፥ እንስሶቻችሁም፥ ትጠጣላችሁ። 18 ይህ በእግዚአብሔር ዐይን ቀላል ነገር ነውና፤ ደግሞም ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣል። 19 የተመሸጉትንም ከተሞች ሁሉ ትመታላችሁ፤ የሚያምሩትንም ዛፎች ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሞቹንም እርሻዎች ሁሉ በድንጋይ ታበላሻላችሁ።” 20 በነጋውም መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፥ እነሆ፥ ውኃ በኤዶምያስ መንገድ መጣ፤ ምድሪቱም ውኃ ሞላች። 21 ሞዓባውያንም ሁሉ እነዚያ ነገሥታት ሊወጉአቸው እንደ መጡ በሰሙ ጊዜ፥ “ሁላችሁ መሣሪያዎችን ይዛችሁ ርዱን” ብለው በሀገራቸው ሁሉ ጮኹ። ተሰበሰቡም፤ ወጥተውም በተራራው ራስ ላይ ቆሙ። 22 ማልደውም ተነሡ፤ ፀሐይም በውኃው ላይ አንጸባረቀ፤ ሞዓባውያንም በፊታቸው ውኃው እንደ ደም ቀልቶ አዩና፦ 23 “ይህ የጦር ደም ነው፤ እነዚያ ነገሥታት እርስ በርሳቸው ተጋደሉ፤ ባልንጀሮቻቸውንም ገደሉ፤ አሁንም ሞዓብ ሆይ! እንግዲህ ወደ ምርኮህ ሂድ” አሉ። 24 ወደ እስራኤልም ሰፈር በመጡ ጊዜ እስራኤላውያን ተነሥተው ሞዓባውያንን መቱ፤ እነርሱም ከፊታቸው ሸሹ፤ ሞዓባውያንንም እየመቱ ወደ ሀገሩ ውስጥ ገቡ። 25 ከተሞቻቸውንም አፈረሱ፤ በመልካሞቹም እርሻዎቻቸው ሁሉ ላይ እስኪሞሉ ድረስ እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ድንጋይ ይጥል ነበር፤ የውኃውንም ምንጮች ሁሉ ደፈኑ፤ የከተሞቻቸውንም ቅጥር አፈረሱ፤ የሚያምሩትን ዛፎች ሁሉ ቈረጡ፤ ባለ ወንጭፎችም ከብበው መቱአቸው። 26 የሞዓብም ንጉሥ እንደ ገደሉአቸውና ድል እንደነሡአቸው ባየ ጊዜ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰባት መቶ ሰዎችን ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ወደ ኤዶምያስም ንጉሥ ያልፉ ዘንድ ሞከሩ፤ አልቻሉምም። 27 ከዚህ በኋላ በእርሱ ፋንታ ንጉሥ የሚሆነውን የበኵር ልጁን ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በቅጥሩ ላይ አቀረበው። እስራኤልም ታላቅ ጸጸት ተጸጸቱ፤ ከዚያም ርቀው ወደ ምድራቸው ተመለሱ። |