ኤርምያስ 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሴዴቅያስ ለኤርምያስ ያቀረበው ጥያቄ 1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ። 2 እርሱም ሆነ፥ አገልጋዮቹ፥ የሀገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 3 ንጉሡም ሴዴቅያስ፥ “ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ” ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የማሴውን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ። 4 እርሱንም በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር። 5 የፈርዖንም ሠራዊት ከግብፅ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬአቸውን በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ። 6 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 7 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ እነሆ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ ሀገሩ ወደ ግብፅ ይመለሳል። 8 ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል፤ ይይዙአትማል፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል። 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አይሄዱምና፦ ከለዳውያን በርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። 10 ነገር ግን እናንተን የሚወጉትን የከለዳውያንን ጭፍራ ሁሉ ብትመቱ፤ ከእነርሱም ጥቂት ተወግተው ያልሞቱ ቢቀሩ ሁሉ እያንዳንዱ በስፍራው ይነሣሉ፤ ይህቺንም ሀገር በእሳት ያቃጥላሉ።” 11 የከለዳውያንም ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ 12 ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይኖር ዘንድ ወደ ብንያም ሀገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ። 13 በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ ሳሩያ የተባለ በር ጠባቂ በዚያ ነበረ፤ እርሱም፥ “ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው” ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው። 14 ኤርምያስም፥ “ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም” አለ፤ እርሱ ግን አልሰማውም፤ ሳሩያም ኤርምያስን ይዞ ወደ አለቆች አመጣው። 15 አለቆችም በኤርምያስ ላይ ተቈጥተው መቱት፤ የግዞት ቤት አድርገውት ነበርና ወደ ጸሓፊው ወደ ዮናታን ቤት ላኩት። 16 ኤርምያስም ወደ ጕድጓድ ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ ኤርምያስም በዚያ ብዙ ቀን ተቀመጠ። 17 ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ፥ “በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን?” ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም፥ “አዎን አለ፤ ደግሞም በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ” አለው። 18 ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፥ “በግዞት ቤት የጣላችሁኝ አንተን፥ ወይስ አገልጋዮችህን፥ ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው? 19 የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች ሀገር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ? 20 አሁንም አቤቱ ንጉሥ ሆይ! ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሓፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።” 21 ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፤ ኤርምያስንም በግዞት ቤቱ ቅጥር ግቢ አኖሩት፤ እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከውጪ ጋጋሪዎች እያመጡ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በግዞት ቤት ቅጥር ግቢ ተቀምጦ ነበር። |