1 ሳሙኤል 6:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እጁ ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ፥ ከምድራችሁም ይቀልል ዘንድ፥ የእባጫችሁን ምሳሌ፥ ምድራችሁንም የሚያጠፉትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዐይነት ምስሎችን ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፣ ከአማልክታችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አገሩን በማጥፋት ላይ ባሉት ዕባጮችና ዐይጦች ዓይነት ምስሎችን ሠርታችሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ክብር ስጡ። ይህን ካደረጋችሁ እጁን ከእናንተ፥ ከአማልክቶቻችሁና ከምድራችሁ ላይ ያነሣ ይሆናል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አገራችሁን ለማጥፋት በተላኩት አይጦችና እባጮች አምሳል እነዚህን ስጦታዎች ሠርታችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብር መስጠት አለባችሁ፤ ይህን ብታደርጉ ምናልባት እናንተን፥ አማልክታችሁንና ምድራችሁን የሚቀጣበትን መቅሠፍት ያነሣ ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የእባጫችሁንም ምሳሌ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፥ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል። |
ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባንን ይዛችሁ በአደባባዩ ግቡ፤ በቅድስናውም ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።
ቅንነትህን በልቤ ውስጥ አልሰወርሁም፥ ማዳንህንም ተናገርሁ፤ ይቅርታህንና ምሕረትህን ከታላቅ ጉባኤ አልሰወርሁም።
እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብፅም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ በቀልን አደርግባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
አሮንም እጁን ዘረጋ፤ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፤ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ ሀገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ።
እግዚአብሔርም እንዲህ አደረገ፤ የውሻው ዝንብም በፈርዖን ቤት፥ በሹሞቹም ቤቶች ውሰጥ፥ በግብፅም ሀገር ሁሉ መጣ፤ ምድሪቱም ከውሻው ዝንብ የተነሣ ጠፋች።
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወንድምህን አሮንን፦ ‘በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖዎቹ፥ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችንም አውጣ’ ” በለው።
ስለ ግብፅ የተነገረ ራእይ። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፤ የግብፅም የእጆቻቸው ሥራዎች በፊቱ ይዋረዳሉ፤ የግብፃውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
ሳይጨልምባችሁ፥ ጨለማም ባለባቸው ተራሮች እግሮቻችሁ ሳይሰነካከሉ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ በዚያም የሞት ጥላ አለና በጨለማውም ውስጥ ያኖራችኋልና ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ።
በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኀጢአትሽን ብቻ ዕወቂ ይላል እግዚአብሔር።
ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድዳባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ፣ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።
በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።
ዕውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፥ “ሂድ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርብ፤ ይህ ሰው ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን” አሉት።
ኢያሱም አካንን፥ “ልጄ ሆይ! ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፤ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝም” አለው።
በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።
በታላቅ ድምፅም “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውሃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት፤” አለ።
ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፤ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሓ አልገቡም።
ልከውም የፍልስጥኤማውያንን አለቆች ሁሉ ሰብስበው፥ “የእስራኤልን አምላክ ታቦት ስደዱአት፤ እኛንና ሕዝባችንን እንዳትገድል በስፍራዋ ትቀመጥ” አሉ።
ከሄደችም በኋላ የእግዚአብሔር እጅ በከተማዪቱ ላይ መጣች፤ ታላቅ ሁከትም ሆነ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ታላቁንም ታናሹንም መታ፤ የውስጥ አካላቸውንም በእባጭ መታቸው፤ የጌት ሰዎችም የውስጥ አካላቸውን ምስል ሠሩ፥
የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩአት፤ ስለበደል መባእ ካሳ አድርጋችሁ ያቀረባችሁትን የወርቁንም ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቷ አጠገብ አኑሩት፤ ትሄድም ዘንድ ስደዱአት።