ዘኍል 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከግብፅ እስከ ሞዐብ የተደረገ ጕዞ 1 በሙሴና በአሮን እጅ ከሠራዊቶቻቸው ጋር ከግብፅ ከወጡ በኋላ የእስራኤል ልጆች የሰፈሩበት ይህ ነው። 2 ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ተጓዙ የሰፈሩበትን ጻፈ፥ እየተጓዙ ያደሩበት ይህ ነው። 3 በመጀመሪያው ወር ከመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ከግብፃውያን ሁሉ ፊት ከፍ ባለች እጅ ወጡ። 4 በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው። 5 የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ። 6 ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ። 7 ከኤታምም ተጕዘው በኤልሴፎን ፊት ወደ ነበረች በኤሮት በር፤ በመግደሎ ፊት ለፊት ሰፈሩ። 8 ከኤሮትም ፊት ለፊት ተጕዘው በባሕሩ መካከል ወደ ምድረ በዳ ተሻገሩ፤ በኤታምም በረሃ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በምረት ሰፈሩ። 9 ከምረትም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች፥ ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም በውኃ አጠገብ ሰፈሩ። 10 ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ። 11 ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 12 ከሲና ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ። 13 ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ። 14 ከኤሉስም ተጕዘው በራፊድን ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። 15 ከራፊድንም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 16 ከሲና ምድረ በዳም ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ። 17 ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በአቤሮት ሰፈሩ። 18 ከአቤሮትም ተጕዘው በራታማ ሰፈሩ። 19 ከራታማም ተጕዘው በሬሞት ዘፋሬስ ሰፈሩ። 20 ከሬሞት ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ። 21 ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ። 22 ከሪሳም ተጕዘው በመቄላት ሰፈሩ። 23 ከመቄላትም ተጕዘው በሳፋር ሰፈሩ። 24 ከሳፋርም ተጕዘው በካሬደት ሰፈሩ። 25 ከካሬደትም ተጕዘው በመቄሎት ሰፈሩ። 26 ከመቄሎትም ተጕዘው በቀጠአት ሰፈሩ። 27 ከቀጠአትም ተጕዘው በተሪት ሰፈሩ። 28 ከተሪትም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ። 29 ከሚትቃም ተጕዘው በኤሴምና ሰፈሩ። 30 ከኤሴምናም ተጕዘው በመሱሩት ሰፈሩ። 31 ከመሱሩትም ተጕዘው በብንያቅን ሰፈሩ። 32 ከብንያቅንም ተጕዘው በገድገድ ተራራ ሰፈሩ። 33 ከገድገድም ተጕዘው በአጤቤት ሰፈሩ። 34 ከአጤቤትም ተጕዘው በኤብሮና ሰፈሩ። 35 ከኤብሮናም ተጕዘው በጋስዮንጋቤር ሰፈሩ። 36 ከጋስዮንጋቤርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ። ከጺን ምድረ በዳም ተጕዘው በፋራን ምድረ በዳ ሰፈሩ። ይህችም ቃዴስ ናት። 37 ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ። 38 ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፤ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። 39 አሮንም በሖር ተራራ ላይ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሃያ ሦስት ዓመት ነበረ። 40 በከነዓን ምድርም ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ። 41 እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ። 42 ከሴልሞናም ተጕዘው በፌኖ ሰፈሩ። 43 ከፌኖም ተጕዘው በአቦት ሰፈሩ። 44 ከአቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ። 45 ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። 46 ከዲቦንጋድም ተጕዘው በጌልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። 47 ከጌልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉት በአባሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። 48 በናባው ፊት ካሉት ከአባሪም ተራሮችም ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ በኩል ባለው በሞዓብ ምዕራብ ሰፈሩ። 49 በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ምዕራብ ከአሲሞት መካከል እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከመሻገራቸው በፊት የተሰጣቸው መመሪያ 50 እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ በኩል በሞዓብ ምዕራብ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 51 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ 52 በዚያችም ምድር የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ አጥፉአቸው፤ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፤ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ 53 በዚያች ምድር የሚኖሩትንም አጥፍታችሁ በውስጥዋ ኑሩ። ምድሪቱን ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና። 54 ምድሪቱንም ትወርሳላችሁ፤ በየወገኖቻችሁም ትከፋፈሏታላችሁ፤ ለብዙዎች ድርሻቸውን አብዙላቸው፤ ለጥቂቶችም ድርሻቸውን ጥቂት አድርጉ፤ እያንዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ። 55 የሀገሩንም ስዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዐይናችሁ እንደ እሾህ፥ ለጐናችሁም እንደ አሜከላ ይሆኑባችኋል፤ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። 56 እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።” |