ሮሜ 12:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ደግሞም እያንዳንዳችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ እምነት መጠን በትሕትና አስቡ እንጂ ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ ብዬ በተሰጠኝ ጸጋ እነግራችኋለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ እንደሰጣችሁ እምነት መጠን፥ በረጋ አእምሮ አስቡ እንጂ ማሰብ ከሚገባችሁ በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ እናገራለሁና። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን ዐስቡ እንጂ ትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። |
እግዚአብሔር መልካም የሆነውንና ከአንተ የሚፈልገውን ነግሮሃል፤ ይኸውም ፍትሕን እንድትጠብቅ፥ ደግነትን እንድትወድ፥ ከአምላክህ ጋር በትሕትና እንድትመላለስ ነው።
“ፈሪሳዊው ቆሞ እንዲህ ሲል በልቡ ጸለየ፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እኔ እንደ ሌሎች ሰዎች ቀማኛ፥ ግፈኛ አመንዝራ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ፤ ይልቁንም እንደዚህ እንደ ቀራጭ ስላልሆንኩ አመሰግንሃለሁ።
አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም።
ወንድሞቼ ሆይ! “ዐዋቂዎች ነን” ብላችሁ አትመኩ፤ የምነግራችሁ አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም የእስራኤላውያን እምቢተኛነት ለዘለቄታው ሳይሆን አሕዛብ ሁሉ በሙላት ወደ እግዚአብሔር እስኪመጡ ድረስ መሆኑን ነው።
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ራሳችሁን ከፍ ከማድረግ ይልቅ ትዕቢትን አስወግዳችሁ ከድኾች ጋር በአንድነት ኑሩ፤ በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ።
ነገር ግን እኔ አሁን የሆንኩትን ሆኜ የምገኘው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው፤ የተሰጠኝም ጸጋ ያለ ፍሬ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሌሎቹ ይበልጥ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም።
እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም እኔ በጣልኩት መሠረት ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት።
እያንዳንዱ ጌታ በሰጠው ስጦታና እግዚአብሔር በጠራው ጊዜ በነበረበት ሁኔታ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሰጠሁት መመሪያ ይህንኑ ነው።
በእናንተ ላይ ሸክም ሳልሆን ከመቅረቴ በቀር ከሌሎች አብያተ ክርስቲያን እናንተን ያሳነስኳችሁ በምንድን ነው? ይህም ጥፋት ሆኖ ከተቈጠረ ይቅር በሉኝ!
ከነዚህ ከተገለጡልኝ ታላላቅ ነገሮች የተነሣ እንዳልታበይ ሥጋዬን እንደ እሾኽ የሚወጋ ሥቃይ ተሰጠኝ፤ ይህም የሰይጣን መልእክተኛ በመሆን እየጐሸመ በማሠቃየት እንዳልታበይ ያደርገኛል።
የተለያዩት የሰውነት ክፍሎች የሚገጣጠሙት በክርስቶስ ነው፤ አካልም በሙሉ የተያያዘው በመገጣጠሚያዎቹ ነው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ የአካል ክፍል የተመደበለትን ተግባር በሚገባ ሲያከናውን አካል በሙሉ ያድጋል፤ በፍቅርም ይታነጻል።
ኃጢአት በመሥራታችሁና የኃጢአተኛው ሥጋችሁ በክርስቶስ በማመን ባለመገረዙ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል፤ ኃጢአታችሁንም ሁሉ ይቅር ብሎላችኋል።
እንዲሁም ሴቶች ጠጒርን በማሳመር ወይም በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ውድ በሆነ ልብስ በማጌጥ ሳይሆን በማፈርና በትሕትና ተገቢ የሆነ የጨዋ ልብስ ይልበሱ።
የሚያስተምር፥ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያስተምር ያስተምር፤ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሁሉ ነገር ይመሰገናል፤ ክብርና ሥልጣን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።
እንዲሁም እናንተ ጐልማሶች! ለሽማግሌዎች ታዘዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ለብሳችሁ አንዱ ሌላውን ያገልግል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑቶች ግን ጸጋን ይሰጣል” ተብሎ ተጽፎአልና።